loader
 • የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አጠቃላይ መረጃ

  @Tariku   2 years ago
  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • @Tariku   2 years ago
  Sewasewer

  የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በ10 አሰተዳደራዊ ዞኖች፣ በአንድ ልዩ ዞን፣ በ105 ወረዳዎች እና በ78 የከተማ ማዕከሎች የተዋቀረ ነው፡፡ አማርኛ የክልሉ የስራ ቋንቋ ነው፡፡ 

  • የስፍራው አቀማመጥ
   • የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜናዊ-ምዕራብ እና በመሀከለኛው ሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ ሲሆን ክልሉ በሰሜን ከትግራይ ክልል፣ በምስራቅ ከአፋር ክልል፣ በደቡብ ከኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ-ምዕራብ ከቤኒሻንጉል-ጉምዝ ክልል እንዲሁም በደቡብ ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋር ይዋሰናል፡፡



  • የቆዳ ስፋት
   • የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት 170‚752 ስኩ.ኪ.ሜ የሚገመት የቆዳ ስፋት ይሸፍናል፡፡

  • ሰንደቅ ዓላማ



  • ርእሰ ከተማ
   • ባህር ዳር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ ከተማ ነች፡፡


                 ባህር ዳር ከተማ

  • ስነ-ህዝብ
   • በ1994 በተገኘው የህዝብ ቆጠራ መሰረት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ብዛት 13,834,297 ሲሆን ከዚህም ውስጥ 6,947,546 ወንዶች እና 6,886,751 ሴቶች ናቸው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ 1‚265‚315 በከተሞች ኗሪ ሲሆን 12‚568‚982 በገጠራማው የክልሉ ቦታዎች ይኖራል ይህም ከአጠቃላዩ የህዝብ መጠን 90 ከመቶ የሸፍናል፡፡ 
   • በሀይማኖት ረገድም 81.5% የኦርቶዶክስ ክርስትያን፣ 18.1% የእስልምና እና 014% የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነው፡፡ 
   • በብሄር ስብጥር አኳያም 91.2% የአማራ፣ 3% የኦሮሞ፣ 2.7% የአገው/አዊ፣ 1.2% የቅማንት እና 1% የአገው/ካምይር ብሄረሰቦች ይኖራሉ፡፡ 


                  የአማራ ልጃገረድ

  • ዋነኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች
   • በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትከሚገኘው ህዝብ 85% የሚሆነው በግብርና ስራ ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ክልሉ የጤፍ ምርትን በዋነኛነት ከሚያመርቱ ክልሎች አንዱ ነው፣ ከዚህም በተጨማሪ ገብስ፣ ስንዴ፣ የቅባት እህሎች፣ ማሽላ፣ ለውዝ፣ ሽንብራና ባቄላ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረቱ ሰብሎች ናቸው፡፡
   • እንደ ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ እና የሸንኮራ አገዳ የመሳሰሉት የአገዳ ሰብሎችም በሰፊውና በድንግሉ የክልሉ ቆላማ ለም መሬት ላይ ይመረታሉ፡፡
   • ከጣና ሀይቅና  አባይ ወንዝን ከመሳሰሉ ትላልቅ ተፋሰሶች የሚገኘው የውሀ ሀብት ለክልሉ የመስኖ እርሻ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡
   • ከክልሉ የመሬት ሀብት 450‚000 ሄክታር የሚሆነው ለእርሻና ለመስኖ ስራ በተለይም ለፍራፍሬና ለአበባ ምርት የተመቸ ነው፡፡ 

  • የመሬት አቀማመጥ እና የአየር ንብረት
   • የአማራ ክልል ከመሬት አቀማመጥ አንፃር ሲታይ በሁለት ዋናዋና ክፍሎች ይመደባል እነሱም የከፍተኛ ተራራማ አካባቢዎች እና የዝቅተኛ ቦታዎች ናቸው፡፡ 
   • የከፍተኛ ቦታዎቹ ከባህር ጠለል በላይ ከ1‚500 ሜትር በላይ ሲገኙ የክልሉን ሰሜናዊ እና ምስራቃዊ ቦታዎች ይሸፍናሉ፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ቦታዎች በሰንሰላታማ ተራራዎች የተከበቡ ናቸው፡፡
   • በ4620 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የራስ ደጀን ተራራ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ የተራራ ከፍታ ሲሆን፤ 4620 ሜትር ከፍታ ያለው የጉና ተራራ፣ 4184 ሜትር ከፍታ ያለው የጮቄ ተራራ እና 4190 ሜትር ከፍታ ያለው የአቡነ ዮሴፍ ተራራ በዚሁ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው፡፡
   • የዝቅተኛው የክልሉ ክፍል በዋነኛነት የምዕራባዊውንና የምስራቁን አካባቢ የሚሸፍን ሲሆን፤ ከ500 እስከ 1‚500 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ አለው፡፡ 
   • በክልሉ የተለያዩ የአየር ንብረት ያላችው አካባቢዎች ሲገኙ 31% ቆላማ፣ 44% ወይና ደጋማ፣ 25% ደጋማ ቦታዎች ናቸው፡፡
   • በአብዛኛው የክልሉ ቦታዎች አመታዊ አማካኝ የሙቀት መጠን ከ15oc አስከ 21oc ይደርሳል፡፡
   • ክልሉ በሀገሪቱ እስከ 80% የሚደርሰውን የዝናብ መጠን ያስመዘግባል፡፡ ከፍተኛው የዝናብ መጠን በክረምት ወራት የሚመዘገበው ሲሆን፤ ይህም ወራት ከሰኔ አጋማሽ እስከ መስከረም መጀመሪያ ይዘልቃል፡፡ 

  • ወንዞችና ሀይቆች
   • የአማራ ብሄራዊ ክልል በ3 የወንዝ ተፋሰሶች የተከፈለ ነው እነሱም አባይ፣ ተከዜ እና አዋሽ ወንዞች ናቸው፡፡
   • ጥቁር አባይ ከሁሉም ረጅሙ ሲሆን 172‚254 ስኩዌር ኪ.ሜ የቆዳ ስፋት ይሸፍናል፡፡ ይሄው ወንዝ ካርቱም ከሚገኘው ነጭ አባይ ጋር እስኪገናኝ ድረስ ያለው ርዝመት 1‚450 ኪ.ሜትር ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ 800 ኪ.ሜትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያደርገው ጉዞ ነው፡፡


                 የአባይ ወንዝ

   • የተከዜ ወንዝ ወደ 88‚000 ስኩዌር ኪ.ሜትር የቆዳ ስፋት ይሸፍናል፡፡ 
   • ከነዚህ ወንዞች በተጨማሪ አንገረብ፣ ሚሌ፣ ከሰም እና ጀማ የተባሉ ወንዞች በክልሉ የሚገኙ ተፋሰሶች ናቸው፡፡
   • በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋቱ አንደኛ የሆነው የጣና ሀይቅ በዚሁ ክልል ይገኛል፡፡ ይህ ሀይቅ 3‚600 ስኩዌር ኪ.ሜትር ስፋት አለው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ሌሎች በእሳተ ጎመራ አማካኝነት የተፈጠሩ እንደ ዘንገና፣ ጉደና፣ አርዲቦ እና ሎግያ የተባሉ አነስተኛ ሀይቆችም በክልሉ ይገኛሉ፡፡
   • በክልሉ የሚገኙት ሀይቆችና ወንዞች ለሀይድሮ ኤለክትሪክ ሀይል ማመነጪያነት፣ ለመስኖ አገልግሎት እና ለአሳ ማጥመድ የሚሆን እምቅ ቸሎታ ያላቸው ናቸው፡፡

  • የቁም ከብት ሀብት
   • በክልሉ ወደ 9.1 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች፣ 8.4 ሚሊዮን በጎችና ፍየሎች፣ 1.6 ሚሊዮንየጋማ ከብቶች እንዲሁም 8.5 ሚሊዮን ዶሮዎች ይገኛሉ፡፡ ይህም ማለት በሀገሪቱ ከሚገኘው የቁም ከብት 40 ከመቶው በዚህ ክልለ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ትልቅ የቁም ከብት ሀብት ክልሉን ለስጋና ወተት ምርት፣ ለቆዳና ሌጦ ምርት ምቹ ያደርገዋል፡፡

  • የዱር እንስሳት
   • በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሚገኙት እንደ ዋልያ አይቤክስ፣ የሰሜን ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና ሌሎች ብርቅዬ እንስሳት በክልሉ የገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የተለያዩ የአእዋፍ አይነቶች ይኖራሉ፡፡

  •  ማዕድን
   • በአማራ ክልል ውስጥ እንደ ከሰል/ኮል፣ ሼል፣ ላይምስቶን፣ ሊግናይት፣ የኖራ ድንጋይ፣ ሲሊካ፣ ድኝ እና ቤንቶኔት የተባሉ ማእድናት ይገኛሉ፡፡
   • ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የፍልውሀ ምንጮችና የማእድን ውሀዎች በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች ናቸው፡፡

  •  ቱሪዝም እና ቅርሶች
   • በ12ኛው ክፍለ ዘመን የተፈለፈለው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፣ የጎንደር ጥንታዊ ቤተመንግስቶች እና ሌሎችም ታሪካዊ መስህቦች በክልሉ ይገኛሉ፡፡
   • በጣና ሀይቅ ደሴቶች ላይ በሚገኙ ገዳማት ጥንታዊ የግድግዳ ላይ ስእሎች፣ ተጠብቀው የቆዩ የጥንት ነገስታት አፅሞችና ቅሪተ አካሎች እንዲሁም ልዩ ልዩ   የእደ-ጥበብ ውጤቶች ይገኛሉ፡፡


                  ገዳማትን ከያዙት የጣና ሃይቅ ደሴቶች አንዱ የሆነው ፣ ደቅ ደሴት 

   • የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘውን ብርቅዬ እንስሳ ዋልያ አይቤክስን ለመጎብኘት እንዲሁም የተራራ መውጣት ስፖርት ለማካሄድ ከፍተኛ ቁጠር ያለው ቱሪስት የሚሄድበት የቱሪስት መዳረሻ ነው፡፡
   • ኢትዮጵያ ለአለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃ ካስመዘገበቻቸው 8 ቅርሶች ሶስቱ የሚገኙት በዚሁ ክልል ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ቅርሶች ባሻግር የጢስ አባይ ፏፏቴ፣ በሰሜን ሸዋ የሚገኙት ልዩ አፈጣጠር ያላቸው ዋሻዎችና አለቶች አንዲሁም የ"መርጡለ ማርያም" ቤተክርስትያን ሌሎች የቱሪስት መስህቦች ናቸው፡፡


                 ጢሥ አባይ ፏፏቴ


  ምንጭ:-
  • የኢትዮጵያ መንግስት ፖርታል (http://www.ethiopia.gov.et)
  • ማእከላዊ ስታትስቲክስ እጀንሲ (http://www.csa.gov.et)
  • www.maps.google.com

 • loader Loading content ...
 • @Haset   1 year ago
  Sewasewer
  እጥር ምጥን ያለ ጠቃሚ መርጃ ነው! አመስግናለሁ ታሪኩ!
 • @Abigel   1 year ago
  Sewasewer
  thanks for sharing!
 • @Hilina   1 year ago
  Sewasewer
  Thanks for sharing, Tariku!
 • @መርሻ   1 year ago
  Interested in just about everything!
  እናመሰግናለን ታሪኩ!

Load more...