loader
 • የአፍሪካ አሜሪካዊያን አውሮፕላን አብራሪዎች እና ኢትዮጵያ... አስገራሚ ታሪክ!

  @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer


  ናይጀል ቢንስ የብዙ ታላላቅና ዝነኛ ሰዎችን ምስል እንዲሁም ታሪካዊ ሃውልቶችን በመቅረጽ ራሱ ዝነኛ መሆን የቻለ Sculptor... ቀራጺ ነው። በአንድ አጋጣሚ ከቴድ ዓለማየሁ ጋር ሆነን አገኘነውና ስለ ሰራቸውና ወደፊት ሊሰራቸው ስላቀዳቸው ነገሮች ሲነግረን ተማረክን። በተለይ ኢትዮጵያ ላይ ሊያቆመው ስለሚፈልገው ጥልቅ ፍልስፍና ያለው ግዙፍ ሃውልት (ላንድማርክ) ሲነግረን ተደሰትን። በመቀጠልም የሚሰራበትን ቦታ እንድንጎበኝለት ጋበዘንና ግብዣውን ተቀብለን ጎበኘነው። 
  ናይጀል ሰዓሊ፥ ቀራጺና ማርሻል አርቲስት ሲሆን በማርሻል አርቲስትነቱም በጃኪ ቻን The Big Brawl ፊልም ላይ ተሳትፏል። የማይክል ጃክሰን አጃቢ ሆኖም ሰርቷል። በሰዓሊነትና በቀራጺነትም በብዙ ቦታዎች አሻራዎቹን አሳርፏል። በቅርቡ በአዲስ አበባ (በኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ) ታሪካዊ ሃውልት ለማስቀመጥም ሽርጉድ ላይ ነው። ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝም ይሄው ታሪካዊ ሃውልት ነው። ናይጀል ቢንስ አሜሪካዊ ቢሆንም ልቡ ያለው ግን አፍሪካ... በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደሆነ በመኖሪያ ቤቱና በወርክሾፑ ውስጥ ካሉት የስዕልና የቅርጻ ቅርጽ ስራዎቹ መመልከት ችያለሁ። አፍሪካ ላይ ለመስራት ባቀደው ትልቅ ሃውልት (ላንድማርክ) አማካይነት ስለ ናይጀል ወደፊት ብዙ እንሰማለን። ለዛሬ ግን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚልከው ታሪካዊ ቅርጽ (ሃውልት) ልንገራችሁ...

  በአውሮፕላን በረራ ታሪክ አፍሪካ አሜሪካዊያን የማብረርና የመዋጋት ችሎታንቸውን ያሳዩት ከ1ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ጀምሮ ቢሆንም በዘረኝነት ምክንያት የአሜሪካ አየር ሃይል እንዳያበሩ ከልክሏቸው ነበር። በመሆኑም በ1ኛው የዓለም ጦርነት ላይ በተዋጊ አውሮፕላን አብራሪነት በመሳተፍ... የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ አብራሪ ሆኖ በታሪክ የሰፈረው ኢጉን ቡላርድ አሜሪካ ማብረር ስትከለክለው የፈረንሳይን አየር ሃይል በመቀላቀል ነበር ተዋግቶ ታሪክ ያስመዘገበው። እንደሱ ወደ ፈረንሳይ ያልሄዱት ወገኖቹ ግን በዘረኝነት ወለድ ጥቁሮችን የመናቅ በሽታ... ውጊያ ላይ መሳተፍ ቀርቶ አውሮፕላን አንስተው ለማሳረፍ እንኳን አሜሪካ እምነት አልጣለችባቸውም ነበር። ይህ የዘረኝነት መድልዎ Tuskegee Institute የተባለውን ዝነኛ የጥቁር ፓይለቶች ማሰልጠኛ መስራች የሆነውን ኮሎኔል ጆን ሲ ሮቢንሰንን ጨምሮ በሁሉም ጥቁር ፓይለቶች ላይ የሚደረግ አሳዛኝ ክስተት ነበር። 
  ነጭ አሜሪካዊያን ፓይለቶች እንደ ወፍ ሰማይ ላይ ሲበሩ ኮለኔል ሮቢንሰንን ጨምሮ አፍሪካ አሜሪካዊያኑ ፓይለቶች ካምፕ ውስጥ ቁጭ ብለው ካርታ እንዲጫወቱ የዘረኝነት ፍርድ ተፈረዶባቸው ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉም ነበር ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረሯን በሬድዮ የሰሙት። እናም የTuskegee Institute መስራቹና የዘር መድልዎውን ለማስቀረት ግንባር ቀደም ታጋይ ፓይለት የነበረው ኮሎኔል ሮቢንሰን ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ ፋሺስት ጣሊያንን ለመዋጋት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚዘምት አስታወቀ።

  አጭር ታሪካዊ ምልሰት (Flashback)

  ጣሊያን በ1888 በአምባ ላጀ፥ በመቐለና በዓድዋ ጦርነቶች በተከታታይ (በሃትሪክ) ከተሸነፈች በኋላ ለ40 ዓመታት ከፍተኛ ዝግጅት አድርጋ... የምድርና የሰማይ ዘመናዊ መሳሪያዎች ታጥቃ ኢትዮጵያን ለመበቀል ስትመጣ በተቃራኒው ሃገራችን በዓድዋው ጦርነት ከነበራት ወታደራዊ ቁመና ብዙ ርቀት አልሄደችም ነበር። (የጣሊያን አውሮፕላኖች ለብቀላ ዓድዋ ከተማን ሲደበድቡ ኢትዮጵያዊያን ከአውሮፕላኖቹ ጋር ለመዋጋት ጎራዴ መምዘዛቸውን ኮሎኔል ሮቢንሰን መስክሯል)

  ኮ/ል ሮቢንሰን በኢትዮጵያ

  ሃገራችን ለጣሊያን ዘመናዊው ብቀላ ፍጹም ባልተዘጋጀችበት ወቅት አሜሪካዊው የጦር አውሮፕላን ፓይለት ኮ/ል ሮቢንሰን የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ለመቀላቀል በጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሳወቀ አጼ ሃይለ ስላሴ ሰምተው የግብዣ ደብዳቤ ላኩለትና ኢትዮጵያ ገባ። 
  የሮቢንሰን መቀላቀልም ለአየር ሃይላችን ከፍተኛ የሞራል መነቃቃተን ፈጠረ። ሮቢንሰን አየር ሃይላችንን ከማደራጀት እስከ መዋጋት ድረስ አኩሪ ታሪኮችን አስመዝግቧል። የኢትዮጵያ ጀብዱም በአሜሪካ ሚዲያዎች ይዘገብለት ነበር። በዘገባ ብቻም አላበቃም የኮ/ል ሮቢንሰን የኢትዮ - ጣሊያን ውጊያ ተሳትፎና ጀግንነት አሜሪካ በጥቁር አሜሪካዊያን ፓይለቶች ላይ የነበራትን የዘረኝነት ማዕቀብ እንድታነሳም ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ራሱ ኮ/ል ሮቢንሰን በመሰረተው Tuskegee Institute የሰለጠኑትና The Tuskegee Airmen በመባል የሚታወቁት ጥቁር ፓይለቶች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ አስደናቂ የጀግንነት ታሪክ ሊያስመዘግቡ ችለዋል። ታሪካቸውም እንደ Red Tails ለመሳሰሉ ታሪካዊ ፊልሞች መነሻ ሆኗል። 
  አሜሪካኖቹም ሆኑ እኛ ብዙ ያልዘመርንለት ኮ/ል ሮቢንሰን ከኢትዮ - ጣሊያን ጦርነት በኋላም በኢትዮጵያ አየር ሃይልና በኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሏል። 
  የማብረር ነጻነቱን በማጎናጸፍ ለሌሎች መሰል ወንድሞቹም የነጻነት ምክንያት እንዲሆን ላደረገችው... ኢትዮጵያ የነበረው ፍቅርም እስከ መቃብር ሆነ። የሚያሳዝነው ግን የቀበርነው አስክሬኑን ብቻ ሳይሆን ታሪኩም ጭምር ነበርና ገና አሁን ታሪኩም፥ የመቃብር ስፍራውም ተቆፍሮ እየወጣ ይገኛል። 
  ሰዓሊና ቀራጺ ናይጀል ቢንስ ለኮ/ል ጆን ሲ ሮቢንሰን መታሰቢያ የሰራው ሃውልት ከጥቂት ቀናት በኋላ ኢትዮጵያ ይደርሳል።

 • loader Loading content ...

Load more...