loader
 • የጃንሜዳ ጨዋታዎች

  @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • @Befkadu Getachew   2 years ago
  Sewasewer


  …..በበቀለ ታዬ……
  :
  (ይህ ጽሁፍ የጥምቀት በአል ከሰአት በኋላ ላይ ጽፌዉ ሳልፖስተዉ ረስቼዉ የነበረ ሲሆን የሚነበብ ካጣችሁ ብቻ ለዛሬ ተደበሩበት በ“በቀለ ታዬ“ ያልኩትም ለደህንነቴ ስል እንጂ ጸሃፊዉስ እኔዉ ነኝ )
  በጥምቀት ጥዋት አልጋዬ ላይ ሆኜ የጄምስ ብራዉንን “ፕሊስ ፕሊስ“ የሚለዉን የ1950 ዎቹ ተወዳጅ ዜማ እያዳመጥኩ ነበር፡፡ ከሳሎን ኢቲቪ ሲያላዝን ይሰማኛል፡፡ግን የኢቲቪ ሰዎች ሁል ግዜ አንድ አይነት ልፍለፋ አይሰለቻቸዉም….አንድ ዜማ …አንድ ቅኝት…… 
  አንዳንዴ ሳስበዉ ኢቲቪ አዝማሪ ቢሆን የሆነ ማሲንቆዉን ይዞ
  “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ 
  …“በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ …
  “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ 
  አሁንስ ወደ ቀጣዩ ግጥም ሊያልፍ ነዉ ስትሉ 
  “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ 
  “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ 
  እያለ ቀኑን ሙሉ ሙዝዝ የሚል ልጋጋም አዝማሪ ይመስለኛል……“ፕሊስ ፕሊስ“ የጀምስ ብራዉን ዘፈን ከ ሸክላ ላይ ባይሆንም ሸክላ ላይ ከተቀመጠዉ ፍላሽ ማጫወቻ በለሆሳስ ይወጣል……...እኔም ሳላዉቀዉ ኢቲቪን ይሁን መንግስትን ይሁን አምላክን ይሁን ብቻ የሆነ ለራሴ ያላወኩትን የሆነ አካል “ፕሊስ….ፕሊስ“ እያልኩኝ ነዉ (ያዉ በዉስጤ ነዉ ታዲያ) 
  “ኤጭ ኢቲቪ!“ ብዬ ወደ ጃንሜዳ ለመሄድ ተነሳሁ፡፡ቲቪዉን ልዘጋዉ ስል “ጠ/ሚኒሲቴር መለስ ዜናዊ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ቦታ የሚሠጣቸዉ መሪ እንደነበሩ አንድ ሰዉዬ የጻፈዉ መጽሀፍ አመለከተ“ ይላል ዜናዉ ፡፡ እና ምን ይጠበስ!? 
  አንድ ነጭ እንደዚህ ብሎ ስለጻፈ መወራት አለበት?! እስቲ አስቡት በናታችሁ…. ባለፈዉ አንድ ከአሌክስ አብርሃ ብሎግ ያነሰ ፎሎወር ያለዉ የአፍሪካ መጽኄት ጠ/ሚ ሃይለማሪያምን የአፍሪካ ምርጡ መሪ ብሎ መረጣቸዉ ሲባል ሰምተን “አሁን ይሄ ዜና ነዉ?!“ ብለን ሼም ይዞን ሰነበትን….. አንዳንዴ “እነኚህ ሰዎች አሁንም ጫካ ያሉ ነዉ እንዴ የሚመስላቸዉ?!“ እላለሁ(በሆዴ) ፡ ማለቴ ኢትዮጲያን የሚያህል ትልቅ እና ታሪካዊ ሀገር መሪ አንድ ተራ ነጭ ሰዉዬ በጻፈዉ መጽሀፍ ዉስጥ መወደሱ በሀገሪቷ “ዋና“ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ “ሄድ ላይን“ መሆን ነበረበት?! እንዲህ አይነት ሪኮግኒሽን የሚያስደስተዉ እኮ የሆነ የ“ጎሬላ ፋይተር“ መሪን እንጂ እንደ ኢትዮጲያ አይነቷን ታላቅ ሀገር የሚመራን መሪ አይደለም…አረ ጎበዝ ለራሳችን ክብር እንስጥ!በሌላዉ አለም ስለ አጼ ሃይለስላሴ የሚባለዉን ብንሰማ ይህ ዜና እንዴት ዜና እንደማይሆን እና እኔ ምን እንደዚህ እንደሚያንጨረጨረኝ ይገባን ነበር! 
  ቀጠለ ዜናዉ “ኢቲቪ ሃምሳኛ አመቱን ሲያከብር ከሰራዊት ፍቅሬ ጋር በመተባበር መሆኑን ገለጸ“ አሉ ደግሞ፡፡ እሺ! ይህ እንኳን አሪፍ ማች ነዉ ……እኒህ ሁለቱ አብረዉ ማዝገም ይችላሉ…….
  ኢቲቪ እንደተለመደዉ የጥምቀት በአልን በተመለከተ የሆኑ ነጠላ(ሲንጉላር) የለበሱ ነጮች ጮክ ብለዉ ብዙም እንግሊዝኛ ከማይችሉ የኢትዮጲያ ጋዜጠኞች ጋር ሲያወሩ እያሳየ ነዉ፡፡ ያዉ ለባለፉት 15 አመታት ከጃሜዳ እንዳደስተላለፈዉ ማለት ነዉ፡፡ ኤጭ “በጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ“ ቀጠለ…..
  “እኔ ግን ምን አዳረቀኝ?!“ ብዬ በቀጥታ ትላንት የሸኘሁትን የአጥቢያዬን ታቦት ለመመለስ ወደ ጃን ሜዳ አቀናሁ (ለደህንነቴ ሲባል የአጥቢያዬ ታቦት ማን እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥቤያለሁ …ኡራኤልን! ሚስጥረኛ ለመሆን ሳይሆን የሴኩሪቲ ነገር ሆኖብኝ ነዉ!) ጃንሜዳ ስደርስ የሰዉ ብዛት የጸበል መጠመቂያዉ ጋር አያስደርስም…በጃንሜዳ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ክብ ሰርተዉ ይጫወታሉ (የተለያዩ ያልኩት የተለያዩ የራያ ግሩፖችን እንጂ እዉነቱን ለመናገር ሌላ “ብሄረሰቦችስ“ አላየሁም)
  ከጭፈራዎች ሌላ ብዙ አይነት ምርጫ ቦርድ ያዘጋጃቸዉ የሚመስሉ ጫወታዎች(ቁማሮች) አሉ፡፡ ለምሳሌ የሆነች ጠባብ ቀለበትን ወርዉሮ በጠርሙስ አንገት ማስገባት ፡ እጅግ በጣም እሩቅ ከሆነ ቦታ ላይ አንዲት ግማሽ ሌትር የምትይዝ ሃይላንድን በኳስ መምታት ፡ አይን ታስሮ የሆነ የተንጠለጠለ ማሰሮ በዱላ ሄዶ መስበር ወ.ዘ.ተ ወዘተ ናቸዉ፡፡ ጨወታዎቹ የተሳታፊዉን ሳንቲም ከመብላት ዉጪ ተሳታፊዉ የሚያሸንፍበት እድል ጠባብ ስለሆነ ነዉ “ምርጫ ቦርድ ያዘጋጃቸዉ ይመስላሉ“ ያልኩት፡፡ ይህን ነጥብ እመለስበታለሁ ግን በዚህ አጋጣሚ ዚስ ዴይስ የጀመረኝን ሁሉንም ነገር ፖለቲሳይዝ የማድረግ ሱስ ልንገራችሁ....
  ባለፈዉ የገና ዋዜማ የነብስ አባታችን እቤት መጥተዉ በዋናነት ፖለቲካ መጻፍ እንዳቆም በሚያጠነጥን ሀሳብ ላይ ማብራሪያ እየሠጡ በዛዉም ስለ ገና እና ስለ ጌታ ዉልደት አንዳንድ ነገሮች እየነገሩን ነበር፡፡ሚስቴ በመሀል እምጵጽ ….እምጵጽ ትላለች ፡፡ በነገራችን ላይ ስብከቱ ዉስጥ ምንም እምጵጽ የሚያስብል ነገር የለም፡፡
  “ይሄዉላችሁ ልጆቼ የጌታን ዉልደት ልብ ብላችሁ ካያችሁት ብዙ ነገር መማር ትችላላችሁ“ አሉ አባ ከፊታቸዉ እጅ በደረት አድርገን ለምንሰማቸዉ እኔና ባለቤቴ…. “ጌታ በቤተመንግስት እንደሚወለድ ሲጠብቁት እሱ ግን በከብቶች በረት ነዉ የተወለደዉ“ አሉ…. ሚስቴ እምጵጽ ትላለች…(የእኔ አእምሮ ግን የሚያስበዉ ግን ቤተ-መንግስት ከሚለዉ በመነሳት ስለ ሌላ ፖለቲካ ነበር) … ቀጠሉ አባ …“ስንት የተከበረ ሙያ እያለ ከድንጋይ ጠራቢ ቤተሰብ ተወለደ….እንዲወለድበት የመረጠዉ ወር ራሱ ልብ ብላችሁ ካያችሁት ከወራት ሁሉ አስከፊዉን ዲሴምበርን ነዉ! ከተወለደ በኋላ በበረት ዉስጥ በትንፋሽዋ ያሞቀችዉ አህያ ከእንስሳት ሁሉ የተናቀች ነች! እዩት ጌታ የሚመርጠዉን !“አሉ የእኔ አእምሮ ደግሞ “ በዚህ አይነት ጌታ ኢሃዲግን ሳይወድ አይቀርማ!“ የሚል የጅል የፖለቲካ ሀሳብ ያስባል…..መጥፎ ሱስ ይዞኛል፡፡
  እና ወደ ጃንሜዳ ጫወታዎች እንመለስ ……. “በአንድ ብር አስር ብር ያሸንፉ!“ ይላል የሃይላንድ ጠርሙስ በኳስ ከረጅም እርቀት ላይ የመምታት ቁማር የሚያጫዉተዉ ልጅ፡፡ኳሷ ያለችበትን እርቀት ብታዩት እንኳንስ ምእመኑ ሮናልዶና ሜሲም ተመካክረዉ ቢመቱ ሃይላንዷን አያገኟትም፡፡በአጭበርባሪነታቸዉ ተናድጄ አንድ ብሬን መዥረጥ አድርጌ ኳሷን ተቀበልኩ እና አነጣጥሬ መታሁ፡፡መቼም የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ እኔዉ ስለሆንኩ በዛ ላይ ሃይላንዷን ሜሲም እንኳን አያገኛትም ስላልኩ አታምኑኝም እንጂ በእልህም ጭምር ስለመታኋት ነዉ መሰለኝ እኔም ሳትኳት፡፡
  “ሌቦች!“ ብዬ ወደ ሌላ ግሩፕ አለፍኩ፡፡ የሆኑ ወጣቶች አርሞኒካ እየነፉ ይጫወታሉ፡፡ ሁሌም ግርም የሚለኝ አርሞኒካ አሁን የት እንደሚሸጥ እና ልጆቹ የሚጫወቷት ዜማ ከአዉራጃ አዉራጃ (የድሮ ስርአት ናፋቂ መሆኔን ልብ ይሏል) አንድ መሆኗ ነዉ ፡፡ 
  እነኚህንም ትቻቸዉ ወደ ሌላ ግሩፕ አለፍኩ፡፡ እዚህኛዉ ጨወታ ላይ ተሳታፊዉ አይኑ በጨርቅ እንደታሰረ ማሰሮዋን መስበር ከቻለ አጫዋቹ እንደነገረን ማሰሮዉ ዉስጥ ያለዉን ሰማንያ ብር ይወስዳል፡፡ 
  እኔ ስደርስ የሆነች ልጅ አይኗ በጨርቅ እየታሰረ ነበር፡፡ ሰዉ ሁሉ ከቦ በጉጉት ያያል፡፡ ልጅቷ የማሰሮዉ አቅጣጫ እንዲጠፋባት አይኗን ያሰረዉ ልጅ ሶስት ግዜ አሽከርክሮ አሽከርክሮ ለቀቃት፡፡ ዱላዋን እያወዛወዘች ማሰሮዉ ይገኝበታል ብላ ወደ አሰበችዉ አቅጣጫ ተጓዘች፡፡ጨዋታዉ በብዙ መልኩ የኢትዮጲያ ብሄራዊ ምርጫን ይመስላል፡፡ መንግስት ለህዝቡ እንደ ተሰቀለቸው ማሰሮ “በምርጫ ልታወርደኝ ትችላለህ“ ብሎ በዱላ መልክ የምርጫ ካርድ ሰጥቶታል፡፡ከምርጫዉ በፊት ግን አሁን ልጅቷን እንዳደረጓት አይነት ህዝቡ የሚፈልገዉን ፓርቲ እንዳያዉቅ አይኑን በጨርቅ ያስረዋል ከዛም ልክ እንደልጅቷ አሽከርክሮ አሽከርክሮ (ያዉ ተስፋ ያላቸዉን በማሳደድ እና በማዋከብ ተስፋ አስቆርጦ ሲያበቃ ) “በል መርጠህ ምታ“ ብሎ ይለቀዋል፡፡
  በነገራችን ላይ ልጅቷ በቀጥታ ወደ ማሰሮዉ አቅጣጫ እየገሰገሰች ነዉ፡፡
  ዙሪያዋን የከበባት ህዝብ እኔን ጨምሮ “በርቺ በርቺ!“ እያለ በትክክለኛ አቅጣጫ እንደሆነች እና መስመሯን እንዳትስት በመንገር ማበረታት ቀጠልን፡፡ግማሹ “ወደ ቀኝ!“ ይላል ግማሹ “ወደ ግራ ብራቮ በርቺ!“ ይላል፡፡ ልጅቷ ቆም ብላ ህዝቡ የሚላትን ለመስማት ስትሞክር የበለጠ ግራ ይገባታል፡፡የሕዝቡ ምክር እና የልጅቷ ግራ መጋባት የምርጫ ሰሞን የሚወጡ ጋዜጦችን እና የ97 ቱን ቅንጅት አስታወሰኝ፡፡ ልጅቷ ቀጥ ብላ ወደ ማሰሮዉ ተጠጋች፡፡ማሰሮዉን ልታነካክተዉ ስትል አጫዋቾቹ ጨነቃቸዉ መሰለኝ ከመካከላቸዉ እንደኛዉ ቀጥ ብሎ ሄዶ ክንዷን ያዘና አሽከርክሯት ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ መራትና ተመለሰ ፡፡
  “እንዴ ይሄማ ፌይር አይደለም!“ ብለን ቀወጥነዉ፡፡ ገንዘብ ለሚሰበስበዉ ልጅ “እንዴት እንዲህ ታደርጋላችሁ!“ ብዬ ቅሬታ አቀረብኩ፡፡ የመለስናት ጥፋት ስላጠፋች ነዉ ብሎ የሆነ የጸረ ሽብር አዋጁን የሚስል ህግ ጠቀሰና የመለሳትም ልጅ ምንም እንዳለጠፋ ገልጾልኝ ፍጥጥ ብሎ አየኝ…የሆነ ነገሩ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን ይመስላል፡፡
  ልጅቷ ግን የዋዛ አይደለችም፡፡ እንደምንም ብላ የማሰሮዉን አቅጣጫ ይዛ ጥረቷን ቀጠለች፡፡ ማሰሮዉን ያገኘችዉ ሲመስላት ባለ በሌለ ሃይሏ ዥዉ ታደርጋለች፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብ ልክ እንደዚህ አይኗን የታሰረች ልጅ ይመስለኛል፡፡ ዱላዉን እያወዛወዘ ጨቁኖኛል የሚለዉን መንግስትን አነክቶ ለመጣል ይፈልጋል…… መአት ጩኸት ከዚህም ከዚያም ይሰማል…..የደረሰበት ሲመሰለዉ ዥዉ ያደርጋል! ግን አያገኘዉም!……. ልጅቷ በሚገርም ፍጥነት ወደ ማሰሮዉ እየተጠጋች ነዉ…….ጩኸቱ በርክቷል…… ጋይስ እኔ የምሸኘዉ ታቦት ተነስቷል እንጂ ይህንን ወሬ ብንጨርሰዉ ደስ ይለኝ ነበር ….“አንባቢ ሆይ ልጅቷና ህዝቡ ይህንን ባዶ እንስራ ያገኙት ይሆን!?“ ….ሌላ ቀን እንመለስበታለን.....
  .ይመቻችሁ
 • loader Loading content ...

Load more...