loader
 • የፈረስ ስሞችና ትርጉማቸው።

  @Demoze   1 year ago
  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • @Demoze   1 year ago
  Sewasewer
  የኢትዮጵያ ነገስታት እና መሳፍንት፣ መኳንንትና ጀግና ሁሉም ፈረስ የመቀመጥ ሙያ አላቸው። እንደውም ጥንት በጨዋ ልጅ አስተዳደግ ውስጥ አንደኛውን ደረጃ ይዞ ክብርም ማዕረግም ያሰት እንደነበረ የታወቀ ነው።

  ስለዚህም በፈረስ ስም መጠራት የተለመደ ፈሊጥ ሆኖ ኖሯል። ይህ አይነቱ ዘዬ በሃገራችን በገባው ግን የኦሮሞዎችን ልማድ በመከተል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሆነ ይነገራል። ሴቶች እንደ ወንዶች የጅግንነት ስራ ለመስራት ቢችሉም እስካሁን በፈረስ ስም ተጠርተው አያውቁም።

  የፈረስ ስም አባ ወይም አባት የሚለውን ቃል በማስቀደም ባንዲት ቃል ብቻ የተነገረ ቢሆንም ጠለቅ ብለው ሲመረምሩት፣ የባለፈረሱን የጠባይ ሁናቴ ምኞቱን ጭምር አጠቃሎ የሚያሳይ ሰፊ ትርጉምና መግለጫ የያዘ ሆኖ ይገኛል። ቅፅል ስሙ የሚሰጠው በቀጥታ ለፈረሱ ቢሆንም የባሌቤቱን ሙያ የሚገልፅና የሚያሞግስ ስለሆነ ጌትዮውን የሚያኮራ ነው። የፈረስ ስም እንደ ስመ ጥምቀት ወይም አለማዊ ስም በካህናት ወይም ባባትና በናት የሚሰየም አይደለም። በመሰረቱ ሲመለከቱት፣ አንድ መስፍን ወይም መኮንን በሰላም ጊዜ ባስተዳደር፣ በዳኝነትና በምክር፤ በጦርነት ጊዜ በጀግንነት እና በዘዴ፣ የሚያሳየውን ደግነትና ርህራሄ፣ ሃይልና ቅልጥፍና፤ በማመዛዘን ከባልደረቦቹ ወይም ከሌሎቹ የሚሰጠው የመታወቂያ ምልክት ነው። አንዳንድ ጊዜም ትንቢትን ያዘለ ሆኖ ይታያል፤ ሆኖም የሁሉም የፈረስ ስም በጦር ባልደረቦች የወጣ ነው ለማለት አያስደፍርም። ምክንያቱም አዝማሪዎችና ችሮታ ፈላጊዎች የሰጪን ልብ ለመሳብና እጁንም ለማስፈታት አንዳንድ ጊዜ አባ ባህር፣ አባ ዝናብ፣ አባ መንዝር፣ የማለት ፈሊጥን መጠቀሚያ አድርገውት እንደነበረ ስለሚታወቅ ነው።

  ከዚህም ሌላ ራሱ ባለጉዳዩ ምኞቱንና ፍላጎቱን ለመግለፅ ሲል መርጦ ያናገረውም እንደማይጠፋ ይታመናል።

  አንድ ሰው የፈረስ ስም ቢኖረውም ለዘወትር መጠሪያው አድርጎ አይጠቀምበትም። ይሁን እንጂ በሰልፍና ባዳራሽ ግብር ይልቁንም በጦርነት ጊዜ፤ በንጉሱ ወይም ባለቃው ፊት እየተንጎራደደ በጓደኞቹ መካከል ሲፎክር ማንነቱን የሚገልፀውና የሚያስተዋውቀው የጎበዝ ስሙን እየጠራ ነው። የእገሌ ጌታ እያለ ፈረስን ማሞገስ፣ ራስንም ማንቆለጳጰስ የተለመደ ፈሊጥ ነው።

  አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በድንገት ያልታሰበ ድምፅ ሲሰማ፣ ለምሳሌ መድፍ ሲተኮስ፣ ዲናሚት ሲፈነዳ፣ ጠመንጃ ሲጮህ፣ መብረቅ ሲበርቅ፣ የእገሌ ጌታ በማለት አፈፍ ብሎ መፎከርም በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ ወኔ የሚቆጠር ነው።

  በማስተዋል ሲመለከቱትም ከሰው ወኔ ጋር የሚቀሰቀስና የሚተባበር ስም ነው ለማለት ያስደፍራል። አንድ ነገር ባማቱት ወይም ባፋጩት ጊዜ ድምፅ እንደሚሰጥ ሁሉ፣ እንዲሁም የጀግና ስሜት ሲቀሰቀስ የሚፈጠር ወይም የሚገኝ ውጤት ወይም ደግሞ ብልጭታ ነው ብል የተሳሳትኩ ኣይመሥለኝም። ባልደረቦችና ሎሌዎችም ልዩ ልዩ የሆኑትን ያለቆቻቸውንና የጌቶቻቸውን የፈረስ ስም እየጠቀሱ መፎከር ልማዳቸው ነው።

  ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎችም ተመሳሳይ የሆነ የፈረስ ስም ሊኖራቸው ይችላል፤ ይኸውም ባጋጣሚነት እንጂ የዝምድና ምልክት ሆኖ አይደለም። እንዲያውም ሰዎቹ ላይተዋወቁ ይችላሉ። በሞክሼ የሚጠሩት ግን በጠባይና በተግባር የሚያቀርርቧቸው ነገሮች በመካከላቸው በተገኙ ጊዜ ብቻ ነው። ለምሳሌ፣ አንዳንዶቹ ለነገ የማይሉ ደፋር ቆራጥ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ የሚያስከትለውን የሚገምቱና የሚያመዛዝኑ ይሆናሉ፤ አንዳንዶቹ ማብላት ማጠጣት ሲወዱ፤ አንዳንዶቹ የመሳሪያና የገንዘብ ስጦታ ማድረግን ይመርጣሉ፤ አንዳንዶቹ ጨካኞች ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ሩህሩህ ይሆናሉ፤ ያንዳንዶቹ መንፈስ ለዳኝነት ሲያዘነብል፣ የሌሎቹ ተቃራኒ ይሆናል።

  በዚህ አይነት ጠባያቸው በመራቸው ተግባራቸውን የሚፈፅሙ አያሌዎች ናቸው። ስለዚህ ነው በባህሪይ የሚቀራረቡት ሁሉ ተመሳሳይ በሆነ የፈረስ ስም ሲጠሩ የምንሰማው። የሚበልጠው ጊዜ ለፈረስ ስም የሚመረጡት ስሞች የወታደርን ወኔ የሚቀሰቅሱ ሃይለ ቃላትን የያዙ ናቸው። ሆኖም ያስተዳደር፣ የዳኝነትና የፖለቲካ ሰዎች ለሆኑ የሚወጣው ትእግስትንና ምክርን የሚያስገነዝብ መሆኑን ልንረዳው እንችላለን። አንዳንድ ጊዜም የፈረሱን ቀለም (መልክ) ይከተላል።  ለምሳሌ፤

  • አስተዳደርንና ዳኝነትን የሚያመለክቱ
  አባ ዳኘው
  አባ መቻል
  አባ ይርጋ
  • ለጋስነትንና ችሮታን፣ የተፈጥሮ ባህሪን የሚገልፁ
  አባ መስጠት
  አባ ሙላት
  አባ ባህር
  አባ ምቹ
  • መመስፋፋትን የእድገትን አላማዎች የሚያመለክቱ
  አባ ደርብ
  አባ ይትረፍ
  • ትክለኛነትን፣ መንፈሳዊነትን፣ ጨካኝነትን፣ ተንኮለኝነትን የሚያመለክቱ
  አባ ሚዛን
  አባ  መልዐክ
  አባ ሰይጣን
  • ቁጡነትን፣ ሃይለኛነትን፣ ጀግንነትን የሚያመለክቱ
  አባ ቃኘው
  አባ  ደፋር
  አባ መብረቅ
  አባ ትንታግ
  አባ ቀማው
  አባ ተርቦ
  አባ መርዞ
  • የፈረሶቹን ቀለም (መልክ) የሚያመለክቱ
  አባ ቦራ
  አባ ጉራች
  አባ ሻንቆ
  አባ ዳማ

  እነዚህንም ቀረብ ብለን ጠልቀን እየተነተንን ብንመረምራቸው በውስጠ ዘየ፣ በሚሥጥር ሰንሰለት እየተሳሰሩ ብዙ ትርጉሞችን የያዙ ሆነው እናገኛቸዋለን -- በተለይም መልካም ምኞትን ተጎናፅፈው እናያለን።

  ምንጭ:
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል ስብስብ ስራዎች
 • loader Loading content ...
 • @መርሻ   1 year ago
  Interested in just about everything!
  እናመሰግናለን ደሞዜ! አባ ጉራች እና አባ ሻንቆ ተቀራራቢ ትርጉም ያላቸው የፈረስ ስሞች ይመስሉኛል። ሁለቱም ጥቁር ፈረስን ይገልፃሉ :)

Load more...