loader
  • የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት ማነው? አላማውስ ምን ይመስላል?

    @ቀዮ   2 years ago
    ብልህ እያንዳንዱን አጋጣሚ ከሌሎች ለመማር ይጠቀምበታል!
  • loader Loading content ...
  • @ቀዮ   2 years ago
    ብልህ እያንዳንዱን አጋጣሚ ከሌሎች ለመማር ይጠቀምበታል!
    የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት መስራች ዲ/ ን ዳንዔል ክብረት ሲሆን አላማው ለኢትዮጵያ በጎ የሰሩ እና ለሌሎች አራያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ማበረታታት እና እውቅና መስጠት ነው። የሚከተለው ሃተታ ከበጎ ሰው ድረ-ገፅ ላይ የተወሰደ ሲሆን የድርጅቱን አላማው ባጭሩ ይገልፃል።

    " የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ኢንዱስትሪያሊስቶች፣ የዲፕሎማሲ ሰዎች፣ ወዘተ የማበረታታት፣ የማድነቅ፣ የመሸለምና ዕውቅና የመስጠት ባህል እምብዛም የለንም፡፡ ከዚህ ይልቅ የመተቻቸትና የመናናቅ፣ የመመቀኛኘትና የመጓተት ልማዶች ጎልተው ይታያሉ፡፡ ይህንን መሰሉን ባህል ባለማዳበራችን የተነሣ የሚሠሩ ሰዎች ያመጡትን ለውጥ ዐውቀው ይበልጥ እንዲተጉ፣ ሌሎች ደግሞ የእነርሱን አርአያ ተከትለው ለሀገራቸው እንዲሠሩ አላደረግናቸውም፡፡ ትውልዱም የእርሱን ዘመን ጀግኖች እንዳያገኝ ዕንቅፋት ሆኖበታል፡፡ በዚህም የተነሣ የውጭውን አድናቂና ናፋቂ ሆኗል፡፡ ይህንን ልማድ ለመቅረፍና ሀገራዊ ጀግኖችን ለማውጣት፣ ለመሸለምና ትውልዱ እንዲያውቃቸው ለማድረግ መሥራት የመንግሥት ብቻ ኃላፊነት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ሊፈጽመው የሚገባ የዜግነት ግዴታው ነው፡፡ "


                    የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት መስራች ዲ/ ን ዳንዔል ክብረት

    የበጎ ሰው ሽልማት የተለያዩ ዘርፎችን ያካተተ ሲሆን የሚከተሉት አስር ዋና ዋና የእጩ መጠቆሚያ ዘርፎች ናቸው።

    1. ሰላም:- በዚህ ዘርፍ ለሀገራዊ ሰላም፣ ለሕዝቦች መግባባት፣ ለግጭቶች መፈታት፣ ማኅበረሰቡ ላቅ ያለ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ የሠሩ ይሸለማሉ

    2. ሳይንስ:- በሕክምና፣ በቴክኖሎጂ፣በፊዚክስ፣ በኬሚስሪ፣ በምሕንድስና፣ በአርክቴክቸር፣ ወዘተ የሠሩ ይሸለማሉ

    3. ኪነ ጥበብ:- በልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች በአዲስ መንገድ፣ በልዩ አቀራረብ፣ የሥነ ጽሑፍን ደረጃ ከፍ ያደረጉ፣ በማኅረሰቡ ዘንድ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሥራ የሠሩ፣ ለኪነ ጥበባችን ዕድገት የተጉ ዜጎች ይሸለማሉ ሀ. ፊልም ለ. ሙዚቃ ሐ. ሥነ ጽሑፍ መ. ቴአትር ሠ. ሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ

    4. የበጎ አድራጎት ሥራዎች:- በርዳታና ሰብአዊ አገልግሎት የሠሩ ይሸለማሉ

    5. ግብርና ንግድና የሥራ ፈጠራ:- በንግድ(ቢዝነስ)፣ በግብርና እና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሥራዎች በመፍጠር፣ አዳዲስ የሥራ ሐሳቦችን በማመንጨት የሠሩ ይሸለማሉ

    6. ስፖርት:- በስፖርቱ መስክ አርአያነት ያለውና በጎ ተጽዕኖ የሚያመጣ ሥራ የሠሩ ይሸለማሉ

    7. መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን መወጣት:- በተመደቡበት መንግሥታዊ የኃላፊነት ዘርፍ አርአያ የሚሆን ለውጥ ያመጡና ተገቢውን ሕዝባዊ አገልግሎት የሰጡ

    8. ማኅበራዊ ጥናት:- በማኅበራዊ ጥናት መስክ ተሠማርተው የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ችግሮች የሚፈቱና አዳዲስ ግንዛቤ የሚያመጡ፣ ዕውቀት የሚጨምሩ ላቅ ያሉ ሥራዎችን የሠሩ ይሸለማሉ

    9. ሚዲያና ጋዜጠኝነት፡ በሚዲያና በጋዜጠኝነት መስክ ለውጥ አምጭና በጎ ተጽዕኖ አሳዳሪ ሥራ የሠሩ ይሸለማሉ

    10.  ቅርስና ባሕል:- ቅርስና ባሕልን በመጠበቅ፣ በማስተዋወቅ፣ በመሰነድና ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ በመሥራት ለውጥ ያመጡ ይሸለማሉ፡፡ 
    የሚከተሉት አስራ አምስት ነጥቦች ደግሞ እጩዎችን የመጠቆሚያ መመዘኛዎች ናቸው።

    1. የሚጠቆመው እጩ በሕይወት ያለ ኢትዮጵያዊ ሰው ወይም ተቋም መሆን አለበት
    2. የምንጠቁማቸው ኢትዮጵያውያን በጎ ለውጥ አምጭ የሆነ ሥራ የሠሩ መሆን አለባቸው፣
    3. የዜጎችን ሕይወት በማሻሻልና ሀገርን በማሳደግ ሊጠቀስ የሚችል ነገር ያከናወኑ መሆን አለባቸው፣
    4. አንድ ሰው በተለምዶ ሊሠራው ከሚገባው ወይም ከሚችለው ሥራ ላቅ ያለ ሰብእና የሚታይበት ተግባር የፈጸሙ መሆን አለባቸው፤
    5. በአሠራር፣ በአስተዳደር፣ በጥናትና ምርምር፣ በኪነ ጥበብና በማኅበራዊ አገልግሎት አዲስ መንገድ ያመላከቱ፣ አዲስ አሠራር የዘረጉ መሆን አለባቸው፣
    6. የሀገርና የሕዝብን ችግር የፈታ ተግባር የከወኑ መሆን አለባቸው
    7. በተሠማሩበት መስክ መሥዋዕትነት ጠያቂ ግዳጅን የተወጡ፣ ራሳቸውን ለሀገርና ለወገን የሰጡ መሆን አለባቸው
    8. ይሁነኝ ብለው የሀገርንና የወገንን ስም የሚያስጠራ፣ ታሪካችንን፣ ባሕላችንን፣ ቅርሳችንን አጉልቶ የሚያወጣ የዜጋ ሥራ የሠሩ መሆን አለባቸው
    9. የማኅበረሰቡን ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን ለሌሎች መጥፎ ምሳሌ በሚሆን መንገድ ያልጣሱና ለትውልዱ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ መሆን አለባቸው
    10. በተቻለ መጠን ከዚህ በፊት ሥራቸው ሊነገር፣ ሊዘከርና ሊታወቅ ያልቻለ
    11. ለሀገሪቱ ዕድገትና ሥልጣኔ ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ
    12. ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ብቁ አመራሮችን የሰጡ፣ በአመራሮቻቸውም አካባቢያቸውን፣ ድርጅታቸውንና መሥሪያ ቤታቸውን የለወጡ፣
    13. አዲስ፣ የራሱ ወጥነት ያለውና ያልተደፈረ የሚመስለውን ሥራ ያከናወኑ፣
    14. የሀገሪቱን ክብርና ደረጃ ያስጠበቁ፣ የሀገሪቱንም መብት ያስከበሩ፣
    15. ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ በበጎ ያስጠሩ፣ ስሟን ከፍ ያደረጉ

    ምንጭ:
    የበጎ ሰው የሽልማት ድርጅት ድረ-ገፅ
    http://www.begosew.com/
  • loader Loading content ...