loader
 • ሰውዬው (ፊደል ካስትሮ) እኛና
  ኩባ

  Sewasewer
 • loader Loading content ...
 • Sewasewer


  ከጥቂት አመታት በፊት የታላቅ ወንድማቸውን በትረ ስልጣን የተቆናጠጡት የኩባው ፕሬዚደንት ራውል ካስትሮ ታላቅ ወንድማቸው የትግል አጋራቸውና የቀድሞው የኩባ ፕሬዚደንት ፊደል ካስትሮ በዘጠና አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን በብሄራዊ ቴሌቪዥን ብቅ ብለው ለህዝባቸው መርዶውን አረዱት::

  አለም በሁለት ሃያላን መንደር ማለትም በየሶቭየት ሶሻሊስና በአሜሪካ ኢምፔሪያሊስት ጎራ ተከፍላ በነበረችበት በነዛ ቀውጢ አመታት ውስጥ አብዮተኛው ፊዴል ካስትሮ እንደነ ሆቺሚኒ ከመሳሰሉ ጓደኞቹና ከታናሽ ወንድሙ ጋር በመሆን ነበር ዱር ቤቴ ብሎ የገባው::በወቅቱ ከአንድ መቶ ሃምሳ ኪሎሜትር በላይ ለአሜሪካ የማትርቀውና የእነርሱው አሼሼ ገዳሜ ማቅለጫ የወሲብ መዳሪያ የመጠጥ መራጫ የሃሺሽ ማጨሻ ሃገር የነበረችውን ኩባን ነጻ አውጥቶ ወደ ዋና ከተማዋ ሃቫና ለመገስገስና የስልጣን በትሩን ለመጨበጥ ሲጣደፍ ገና የ32 አመት አፍላ ጎረምሳ ነበር::ፊዴል ካስትሮ የወቅቱን አፍቃሪ አሜሪካውን የባፕቲስታ ስርአት ገርስሶ እንደ አውሮፓውያን ቀመር 1959 የተቆናጠጠውን የስልጣን እርካብ እስከ 2006 አመተ ምህረት ድረስ ሽምጥ ሲጋልበው ከርሞ በአንጀት ህመም ምክንያት ለታናሽ ወንድሙና ለትግል አጋሩ ለራዉል ካስትሮ ስልጣኑን ለማጋራት ተገደደ::ያ ከከንፈሩ ቶስካኖ ሲጃራ የማይለየውና የብዙሃኑ ወጣቶችን በአጫጫሱ ጭምር ቀልብ ይስብ የነበረው ፊዴል ካስትሮ ያንን ተወዳጅ ቅጠልያ ወታደራዊ መለዮውን በዛ ለግላጋ ቁመናውና ሰፊ ደረቱ ላይ ከተገጠገጡት ኒሻኖች ጋር አድርጎ ወደ አደባባይ ብቅ ሲል ግርማ ሞገሱ እጅግ ማራኪ የነበረው ሰው የገመምተኛ ቱታውን አድርጎ ከመኖሪያ ቤቱ የሚውል ግራና ቀኝ ክንዱን ጎበዛዝት ይዘው ወዲህና ወዲያ የሚያዘዋውሩት አዛውንት ሆነና አረፈው::

  ካስትሮ በ2008 አመተ ምህረት ስልጣኑን ለታናሽ ወንድሙ በይፋ ካስረከበ በኋላ በተደጋጋሚ ሞቷል እየተባለ ሲወራበት የነበረ ቢሆንም ሰውየው በዋዛ እጅ የማይሰጥ ነበርና በተደጋጋሚ በብሄራዊው የኩባ ቴሌቭዥን ጣብያ ብቅ እያለ ከዘራ ያልያዘበት እጁን በቡጢ አምሳያ ጨብጦ ሽቅብ ቁልቁል እያደረገ “አለሁ እኖራለሁ እንተያያለን” አይነት ፉከራ እየፎከረ በተደጋጋሚ ሲታይ ነበር::

  ሃገራችን በሶማሊያ ወራሪ ሃይል በተወረረችበት አፍላ የደርግ የስልጣን አመታትም ካስትሮ  አይነተኛ ዉለታ ለኢትዮጵያ ዉሎ እንደነበር በወታደራዊው ቡድን ዉስጥ ስልጣን የነበራቸው የወቅቱ ሹማምንት ዛሬ ዛሬ ጽፈው በሚያስነብቡን መጽሃፍ ልንረዳው ችለናል::በወቅቱ ንጉሰ ነገስት አጼ ሃይለስላሴ የወራሪው የሶማሊያን ጦር ለመመከት ከዚህም ከዚያም ብለው ያሟጠጡትን የሃገሪቱን አንድ መቶ ሚሊየን ዶላር ለአሜሪካን መንግስት ገቢ አድርገው መሳሪያ እንዲሰጧቸው ተደራድረው ነበር::የግዥው ሁኔታ በአግባቡ ሳይካሄድ የየካቲቱ አብዮት ደርሶባቸው ስልጣናቸውን ባጡት ንጉስ ምትክ ስልጣኑን የያዘው የደርግ መንግስትም ቀደም ሲል ክፍያ የተፈጸመበትን መሳሪያ የአሜሪካ መንግስት እንዲሰጠው ተደጋጋሚ ተማጽኖ ቢያደርግም ምላሹ ጆሮ ዳባ ልበስ ሆነበር::በዚህ ግዜ ነበር አፍለኛው የደርግ መንግስት ፊቱን ወደ ምስራቁ ጎራ በማዞር በወቅቱ የሶሻሊስት አቀንቃኝ የነበሩትን እንደነ ሰሜን ኮሪያ ኩባና ሶቭየትህብረትን መጎዳኘት የጀመረው::በወቅቱ ሶቭየት ህብረት በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ጦር ሰራዊት የደርግ መንግስት እንዲገነባ የጦር መሃንዲሶቿን በአማካሪነት ጦር መሳሪያዎቿን ደግሞ በብዛት ወደ ኢትዮጵያ በመላክ መንግስታችንን እስከ አፍንጫው ልታስታጥቀው ችላ ነበር::ነገር ግን የኩባዊያኑ ዉለታ ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነበር::ኩባ ሙሉ ትጥቅ የታጠቁ በበቂ ሁኔታ የሰለጠኑ ፋኖ ወታደሮቿን ከመሳሪያ እርዳታ ጋር አብራ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የላከችው::

  ይህ በስተመጨረሻው ደርግን የልብ ልብ የሰጠው የሶማሊያ ጦርነት በኢትዮጵያ ፍጹም አሸናፊነት በተጠናቀቀበት ወቅት ቁጥራቸው ወደ 15000 የሚጠጉ (ቁጥሩን በተለያዩ  መዛግብት ላይ የተለያየ መጠን መሰጠቱን ልብ ይሏል)የኩባ ወታደሮች ደማቸውን ለኢትዮጵያ ማፍሰሳቸውን መዛግብት ይነግሩናል::ለዚህ መስዋእትነትና ወዳጅነት ሲባል ነበር ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አጠገብ የሚገኘው ባለ ቀይ ኮከቡ የ“ትግላችን”ሃውልት ተመርቆ ለመታሰቢያነት የቆመው::

  ካስትሮና ኩባ ለኢትዮጵያ ከሰጡት ዉለታ ሌላኛው ተጠቃሹ ጉዳይ በወቅቱ የነበረው የትምህርት ስልጠና (SCOLARSHIP)ነበር::ዛሬ ዛሬ በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሰራተኞቻቸውን በገፍ ወደ ቻይና ይልኩ እንደነበረው የቀድሞ መንግስትም ካድሬዎቹንና ብቁ ተማሪዎቹን ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እንዲሁም ወደ ኩባ ይልኩ ነበር::በዚህም የኩባን ዉለታ ዛሬም ድረስ የያኔዎቹ የኩባ ተማሪዎች ያስታዉሳሉ::

  እኝህ በዘጠና አመታቸው ከሰሞኑ መሞታቸው የተነገረን የቀድሞው የኩባ ፕሬዚደንት ፊደል ካስትሮ ኢትዮጵያን ከአንዴም ሁለት ግዜ ጎብኝተው እንደነበር “አብዮቱና ትዝታዬ”በተሰኘው መጽሃፋቸው ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዚደንት ሌተና ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታ ይገልጻሉ::የመጀመሪያው ጉብኝታቸው የነበረው የኢትዮጵያ አብዮት በተካሄዴ በሁለተኛው አመት ገደማ ነበር::ወቅቱ የሶማሌ ወራሪ ጦር ኢትዮጵያን ወሮ ስለነበረና ካስትሮም ከሶማሊያው መሪ ዚያድ ባሬ ጋር ጥሩ ቀረቤታ ስለነበራቸው ሞቃዲሾን ከጎበኙ በኋላ ኢትዮጵያን በመጎብኘት የሽምግልና ስራን ለማከናወን እግረ መንገዳቸውንም የኢትዮጵያን አብዮት አይነቱንና ሁኔታዉን ለመረዳት ነበር ይፋዊ ላልሆነ ጉብኝት በመጋቢት ወር 1969 አመተ ምህረት በአንድ ሻምበል የኩባ ጦር ታጅበው ወደ አዲስ አበባ የመጡት::

  ሌላኛው የካስትሮ ጉብኝት ደግሞ በደርግ ግዛተ መንግስት ሁል ግዜ በድምቀት ይከበር በነበረው የመስከረም ሁለት በአራተኛው የአብዮት በአል ላይ ነው::ለብሄራዊ ክብረ በአሉ እጅግ ከፍተኛ ድምቀት ሰጥተውትም እንደነበር ዛሬም ድረስ የሚታየው ምስላቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል::በወቅቱም በየቀበሌው ይገኙ የነበሩ የደርግ ካድሬዎች ህዝቡ የወቅቱ ዝነኛ የአብዮተኞች ምሳሌ የነበሩትንና ፋኖውን ፊዴል ካስትሮን በነቂስ ወጥቶ እንዲቀበሉት መታዘዙን ተከትሎ የተቀለደው ቀልድ ዛሬም ድረስ ይወራል::

  የመልእክቱ መደበኛ ይዘት የነበረው “የቀበሌ  ነዋሪዎች በሙሉ ፊዴል ካስትሮ ስለሚመጣ ወጥታችሁ ተቀበሉ”ነበር::ነገር ግን በወቅቱ በአንዱ ቀበሌ ይህንን መልእክት እንዲለፍፍ የታዘዘው ጡሩንባ ነፊ እምብዛም በትምህርቱ ያልገፋና ነገር ቶሎ የማይይዝ ስለነበር ፊዴል ካስትሮ የሚለው ስም አልያዝ ብሎት “የቀበሌ ነዋሪዎች በሙሉ “ፍየል ታስሮ” ስለሚመጣ ቢላዋ ይዛችሁ ተቀበሉት”ብሎ ለፈፈ ተብሎ  ሲቀለድ ነበር::ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌላው ተጠቃሽ ቀልድ ደግሞ ኮሎኔል መንግስቱ ለመጀመሪያ ግዜ የኩባውን ፕሬዚደንት በአካል ተገናኙ በተባለበት ግዜ የተቀለደው ቀልድ ነው::በወቅቱ ፊዴል ካስትሮ  አዲስ አበባ እንደገቡ እጃቸውን በመዘርጋት ሙሉ ስማቸውን ጠቅሰው ነበር የተዋወቁት “ፊዴል ካስትሮ ሩዝ እባላለሁ”ባሉበት ግዜ መንግስቱ የሚያውቁት ፊዴል ካስትሮ  እሚለውን ስም ብቻ ስለነበርና የአያት “ሩዝ” የምትለዋ ተቀጥላ ስም ሳይሆን የሃገሪቱን ታዋቂ ምግብ የጠቀሱላቸው መስሏቸው ኮሎኔሉም እጃቸውን ዘርግተው “መንግስቱ ሃይለማርያም ቅንጬ” ብለው መልሰዋል እየተባለ ይወራ ነበር::

  ፊዴል ካስትሮ  እጅግ አወዛጋቢ እና ገራሚ ሰው ናቸው አሜሪካ ሰዉዬውን ለመግደል ያልቧጠጠችው ገደል ያልቆፈረችው ጉድጓድ ያልበጠሰችው ቅጠል ያልማሰችው ስር አልነበረም::ለዚህም አላማዋ የተመረዘ የጥርስ ብሩሽ የተበከለ ሲጃራ  በመርዝ ጭስ የታፈነ ስቱዲዮ ስልጡን እና ገዳይ ስኳዶች እና የመሳሰሉትን በማሰማራት ለ638 ግዜ ሰዉዬውን ልትገድላቸው ብትሞክርም ሳይሳካላት ቀርቶ ካስትሮ  በስልጣን ላይ ለ47 ሰባት አመት ሲቆዩ አስራ አንድ የአሜሪካ ፕሬዚደንቶች ተፈራርቀዋል::

  በ1960 ዎቹ የነበሩ የተማሪ እንቅስቃሴዎች እንደ መሪ መፈክርና እንደ ምሳሌ ሲያደርጓቸው ከነበሩ አብዮቶችና የትጥቅ ትግሎች መካከል የደቡብ አሜሪካዎቹ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሾች ናቸው::ለዚህ ይመስላል “ፋኖ  ተሰማራ ፋኖ  ተሰማራ እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼጉቬራ”እያሉ ሲያዜሙ ይደመጡ የነበረው::እንደሚታወቀው ኤርኔስቶ  ቼጉቬራ ደግሞ ከተወለደበት ሃገር በይበልጥ በሌሎች ሃገሮች የነጻነት ተጋድሎው ስለሚታወቅና በተለይ በኩባ የነጻነት ትግል ባደረገው ጉልህ ተሳትፎ ብሎም ከፊዴል ካስትሮ  ጋር በነበረው የቅርብ ግንኙነት የኢትዮጵያ አብዮተኞች እንደ ምሳሌ ሲያነሱት በተደጋጋሚ ያነሱት ነበር::

  የፊዴል ካስትሮን ነገር ስነነሳ ከቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ከኮሎኔል መንግስቱ ጋር የነበራቸውን እጅግ የጠለቀ ግንኙነት ሳያነሱ መተው ታሪክን ጎምዶ እንደማስቀረት ይቆጠራል::በአስራ ሰባቱ የደርግ አገዛዝ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ከአንዴም ሁለት ግዜ መጥተው የነበሩት ፊዴል ካስትሮ  በ1970 አመተ ምህረት ገደማ የኢትዮጵያን ሉአላዊ ግዛት በእብሪት ወሮ የነበረውን የሶማሊያውን መሪ ሞሃመድ ዚያድባሬንና መንግስቱ ሃይለማርያም ገጽ ለገጽ በማገናኘት ሁለቱ የሶሻሊስት ሃገሮች የድንበር ችግራቸውን በሰላም እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት አድርገው እንደነበር: ነገር ግን በወቅቱ በሶቭየት ህብረት አለኝታነት እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጦር መሳሪያ በመተማመን መንግስቱ ሃይለማርያምን እንደ አንድ “ተራ ሻለቃ” እያጣጣለና ቅኝ ገዝዎች የሰጡትን የ“ታላቋ ሶማሊያ” ካርታ በተደጋጋሚ እንደ ምሳሌ በማንሳት የሰላም ድርድሩ እውን እንዳይሆን ስላደረገ ፊዴል ካስትሮም የዚያድባሬን ትምክህተኝነት በውል ስለተገነዘቡ ነበር ኢትዮጵያን ለመርዳት የወሰኑትና 15000 ወታደሮቻቸውን ህይወት ለመገበር የወሰኑት::

  ሌላው ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩ ደርጎች በወቅቱ የጦር መሳሪያ ፍላጎታቸን ለማሟላት ፊታቸውን ያዞሩት ወደ ሶቭየት ህብረት ነበር::ሶቭየቶችም ጦር መሳሪያውን ከፊሉን በእርዳታ ከፊሉን ደግሞ በረዥም ግዜ ብድር እንዲከፈል ተስማምተው ስለነበር ሲያስታጥቁን የነበረው በወቅቱ በጦርነት ላይ ሌላ ጦርነት የተደራረበበት የደርግ መንግስት የብድሩ መጠን እጅግ በጣም የበዛ ሚሊየን ዶላር መሆኑ ስላሳሰበው በሊቀመንበሩ በኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም አማካይነት ለመፈረም ሲያመነታ ቆየ::ይህንን የኮሎኔል መንግስቱን ፍራቻ የተመለከቱት ፊዴል ካስትሮም “መንግስቱ ሶቭየቶች እኮ ይህንን ሁላ ገንዘብ ችላችሁ እንደማትከፍሉት እያወቁ እኮ  ነው የሚያስፈርሟችሁ የነሱ ጽኑ ፍላጎት የሶሻሊዝም መስፋፋት ነው ብቻ አንተ በርትተህ ሶሻሊዝምን አስፋፋ ምን አለ በለኝ ብድሩን ወይ ይቀንሱታል ወይ ይሽሩታል::ካልሆነ እኛም እናግዝካለን”በማለት ነበር ፕሬዚደንት መንግስቱን ያበረታትቱትና በርካታ የጦር መሳሪያ ባለቤት እንድንሆን ያደረጉን::

  ቁመተ ለግላጋ ፊታቸው የማይፈታ ቆፍጣና ደረተ ሰፊ ወንዳወንድ መነጽር ከአይናቸው ቶስካኖ  ከአፋቸው የሚበዛው ፊዴል ካስትሮ ለሃያላኑ ምእራባዊያን ፈጽሞ ሳይበገሩ እድሜን ጠግበው በለሆሳስ ክንዳቸውን ተትተርሰው እስከወዲያኛው አሸለቡ::አሜሪካ “አምባገነን”እያለች እምትፈርጃቸውን የአለም መሪዎች በአንዱ ይሁን በሌላው መንገድ እየገዘገዘች ስትገነድሳቸው ኖራ የፊዴል ካስትሮ  ጉዳይ ግን አልሆን ብሏት ከረመ::እርሳቸውም ከአሜሪካ ጋር መሰዳደቡና እሰጥ አገባው የተመቻቸው ይመስል ነበር::ምን ያደርጋል እርጅና ጓዙን ይዞ እየተንኳተተ መጣና ከቤት አዋላቸው::እንደፎከሩትም አሜሪካ እጅ ላይ አልወደቁም::እንደ ሌሎች መሪዎችም በገዛ ወታደራቸው አልተገደሉም::በእርጅና ወሮቻቸው ጥቂቶች ብቻ በሚታደሉት መልኩ የህዝብና የመላው አለም ፍቅር አልተለያቸውም ነበር::አሜሪካ እንደሰጠቻቸው የ “አምባገነን”ስያሜ ሬሳቸው እንደ አህያ ሬሳ በየመንገዱ አልተጎተተም::እነሆ ኩባ ዘጠኝ የሃዘን ቀናትን አውጃ የመሪዋን ሞት ማቅ ለብሳ አመድ ነስንሳ ልታከብር ቀናትን እየቆጠረች ባንዲራዋንም ዝቅ አድርጋ እያውለበለበች ነው::እንዲህ ከነስህተቱ በህዝብ ዘንድ እስከ ሞት ድረስ የሚወደድ መሪ ዛሬ በህይወት ይኖር ይሆን::

   (ክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል)

 • loader Loading content ...
 • @እሸቱ አበበ   1 year ago
  Hard core sewasewer who believes in social learning!
  እጅግ በጣም ግሩም የሆነ መጣጥፍ ነው ክቡር! በመህል ጣል፣ ጣል ያደረካቸው ቀልዶች ደግሞ ገዳዮች ናቸው :) "መንግስቱ ሃይለማሪያም ቂንጬ" ... man it made me laugh hard :)
 • @Hilina   1 year ago
  Sewasewer
  Wow, good stuff!! Thanks for sharing, Kibur!
 • @Tesfaye Atew   1 year ago
  Member of Team Sewasew, and believes in social learning!
  አዝናኝ፣ወቅታዊ እና ቁምነገር አስጨባጭ ፅሁፍ ነው፣እጅግ በጣም እናመስግናለን ክቡር!  እንደዚህ አይነት ግሩም ፅሁፍ ማበርከትህን እንደምትቀጥል ተስፋ አለን!!!
 • @Adugna   1 year ago
  Sewasewer
  አሪፍ ነው !
 • @የቆሎ ተማሪ   1 year ago
  ስለምንተ ማሪያም
  ማለፊያ ጽሑፍ!