loader

Topics (133)


loader Loading content ...

Explanations (255)


 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  እንደ እንግሊዝ ጦር አዛዦች አባባል ተልኳቸው የእንግሊዝ እስረኞች ለማስፈታት ነበረ። ከዚህ ተልዕኮ ሽፋን በስተጀርባ ግን አላማቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ታሪካዊ ይዘት ያላቸውን ቅርሶች ለመዝረፍ ጭምር መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም።

  1ኛ: ሪቻርድ ሆምስ የተባለው የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ከእንግሊዝ ጦር ጋር አብሮ እንዲመጣ መደረጉ ለዚህ የዘረፋ ተግባር መሳካት እንደነበረ ግልፅ ነው።

  2ኛ: የእንግሊዝ ወታደሮች በቴዎድሮስ ሬሳ ላይ የተረባረቡት ለምን ይሆን በማለት ራሳችንን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ምናልባትም ሳይማረኩ ራሳቸውን ገድለው በመገኘታቸው የተነሳ በእንግሊዞች በኩል የመበቀል ሁኔታ አንፀባርቆ ሊሆን ይችላል፤ በሰበቡ ግን ዘረፋ መፈፀማቸው አይካድም።

  በአፄ ቴዎድሮስ ገናናነትና አልበገር ባይነት የተነሳ ካሁን አሁን ሽንፈት ይደርስብን ይሆናል በማለት የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸው የእንግሊዝ ወታደሮች የአፄ ቴዎድሮስን መጨረሻ እስካላወቁ ድረስ ለዘረፋ ሊሰማሩ አልቻሉም ነበር። ውሎ አድሮ ግን ንጉሡ ራሳቸውን መግደላቸው በይፋ እንደተገለፀ ወደ ዘረፋ ተግባራቸው በቡድን በመሆን በየአቅጣጫው ተሰማሩ።

  የመጀመሪያው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው በሟቹ ንጉስ ሬሳ ላይ ነበር። የአንገት መስቀልና የጣት ቀለበታቸውን፤ ሸሚዛቸውንና ሽጉጣቸውን ከመዝረፋቸውም ባሻገር ሹሩባቸውን ሳይቀር ሸልተው የወሰዱ ለመሆኑ በታሪክ መዛግብት መረዳት ይቻላል።

  ሁለተኛው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው የቤተመንግስት ህንፃ በመድፈር ነበር። ንጉሡ በሕይወታቸው ሳሉ ብሔራዊ ቤተ መፃህፍት ለማቋቋም የሰበሰቧቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ መፅሐፍቶችን እንደዚሁም ባሁኑ ጊዜ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ የመንግስት ሰነዶችና የተለያዩ መረጃዎችን ሳይቀሩ ዘርፈዋል። ከነዚህም መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶችና ማህተም፣ በተለይም ክብረ ነገስት የተባለው ታላቁ መፅሐፍ ይገኙባቸዋል። ቀጥለውም ወደ ንጉሰ ነገስቱ ማድቤት ውስጥ በመግባት ወደ ሃያ እንስራ የሚሆን የተጠመቀ ጠጅና የእህል አረቄ ጭምር ዘርፈው ከመጠን በላይ ሰክረው ነበር። ከዘረፏቸው ቅርሶች ይልቅ ጥፋት ያደረሱባቸው አመዝነው ታይተዋል። ብዙ ቅርሶች ጥለዋል፣ ሰባብረዋል፣ መፅሃፍትንም ቀዳደዋል፤ አልባሳትንም ሸረካክተዋል።

  የሶስተኛው የዘረፋ ቡድን ከወሰዳቸው መካከል ከወርቅ የተሰራ የአቡነ ሰላማ አክሊል ወይም ዘውድ ጫማና ቀበቶ፣ ከወርቅ የተሰሩ ሁለት ፅዋዎች፣ ከወርቅ የተሰራ በአንገት ላይ የሚጠለቅ የአፄ ቴዎድሮስ የሶሎሞን ኒሻን እንዲሁም ንጉሱ ሲነግሱ ለብሰውት የነበረው የማዕረግ ልብስ ይገኙባቸዋል።

  አራተኛው ቡድን ከዘረፏቸው መካከል የተለያዩ ጋሻዎች፣ ከነዚህም ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚገመተውና የፊታውራሪ ገብርዬ ጋሻ፣ ልዩ ልዩ ጦሮችና ጎራዴዎች፣ ያሸበረቁ የፈረስ እቃዎች፣ በተጨማሪም የቴዎድሮስ እስረኞች የታሰሩበት የእግር ብረት ይገኙበታል።

  አምስተኛውና የመጨረሻው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው አፄ ቴዎድሮስ በየአገሩ ሲዘዋወሩ ያርፉበት በነበረው ድንኳናቸው ይጠጡበት በነበረው ዋንጫቸው፣ የማንነቱ ባልታወቀ የፈረስ ልባብ ላይ ነበረ። ወታደሮቹ በዚህ ሳይገቱ የደረሱበትን መንደር በማሰስና እያንዳንዱ ቤት ውስጥ በመግባት ተመሳሳይ ዘረፋ ከማኬሃዳቸውም ባሻገር ከተለያዩ ቤተክርስቲያኖች የተገኙትን መንፈሳዊ ስዕሎችና እንደዚሁም ቁጥራቸው አስር የሚደርሱ ታቦቶችን ሳይቀሩ ወስደዋል። በአጠቃላይ ከንጉሰ ነገስቱ ቤተመንግስት ጀምሮ በአነስተኛ ጎጆ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ሳይቀሩ ተዘርፈዋል።

  አብዛኞቹ በዘረፋ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ወታደሮች አስተሳሰብ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት እንጂ ለእቃዎቹ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስነት ዋጋ እንዳልሰጧቸው መገመት አያዳግትም። ለምሳሌ፣ ሪቻርድ ሆምስ የብሪትሽ ሙዚየም ኤክስፐርትና አርክዎሎጂስት ከአንድ በዘረፋ ላይ ተሰማርቶ ከነበረ ወታደር ከወርቅ የተሰራውን የአቡነ ሰላማን የዘውድ አክሊልና የወርቅ ፅዋ በላዩ ላይ በግዕዝ እንደሚከተለው የተፃፈበትን "ዝንቱ ፅዋዕ ዘወሃብዋ ዳግማዊ እያሱ ወብእሲቱ ወለተ ጊዮርጊስ ለቅድስት ቁስቋም ከመ ትኩኖሙ መድኃኒተ ስጋ ወነፍስ" ወደ አማርኛ ሲተረጎም "እንዲሁም አፄ ኢያሱ ብርሃን ሰገድ ለቁስቋም ቤተክርስቲያን ያበረከቷቸውን ሶስት ኪሎ የሚመዝኑ የቁርባን ፅዋዎች" ማለት ሲሆን እነዚህንም በአራት የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ እንደሸጡላቸው ይነገራል።

  ጄኔራል ናፒር የወታደሮቹን አስተሳሰብ መነሻ በማድረግ በመቅደላና በአካባቢዋ የተዘረፉት የባህልና የታሪክ ቅርሶቻችን በሙሉ በጫረታ እንዲሸጡ አዘዘ።

  ጨረታውን የተሳካ ለማድረግ ገላጣ በሆነችው ደላንታ ሜዳ እንዲካሄድ ተወሰነ። ቅርሶቹን ከመቅደላ ወደ ደላንታ ለማድረስ በአስራ አምስት ዝሆኖችና ከሁለት መቶ በላይ በሚሆኑ አጋሰሶች ተጠቅመዋል። ይህም የሚነግረን የቱን ያህል ብዛት ያላቸው ቅርሶች ተዘርፈው እንደነበረ ነው።

  ደላንታ እንደደረሱም የተለያዩ ስጋጃዎች ሜዳው ላይ እንዲነጠፉ ተደረገ። በስጋጃዎቹ ላይ ቅርሶቹ በያይነታቸው ተደርድረው ለጫረታ ተዘጋጁ። አጫራችም የሚሆን መኮንን ተመረጠ። ለሽያጭም ከቀረቡት እቃዎች መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር ይገኝበት ነበር።

  ጨረታው ከተጀመረ አንስቶ እስካለቀበት ጊዜ ድረስ በማንም ሊሸነፉ ያልቻሉት ቀደም ሲልም ገና ከሀገራቸው ሲንቀሳቀሱ ገንዘብ አስታቅፈዋቸው ወደ ኢትዮጵያ ተሸኝተው የነበሩት የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሚስተር ሪቻርድ ሆልምስና እንዲሁም ከወታደሮቹ በኩል ኮሎኔል ፍሬዘር ይገኙበታል። ለምሳሌ፣ አፄ ቴዎድሮስ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ይይዙት የነበረው በብር እና በወርቅ ያሸበረቀ ጋሻ የጨረታው መነሻ አስር ፓውንድ ሆኖ እስከ ሁለት መቶ ፓውንድ በመድረስ ኮሎኔል ፍሬዘር የጨረታው አሸናፊ በመሆን ሊገዛው ችሏል።

  ጨረታው ለሁለት ቀናት ያህል ከተካሄደ በኋላ ከሽያጭ የተሰበሰበውን አምስት ሺ ፓውንድ ወታደሮቹ እንዲከፋፈሉት ተደረገ።

  ምንም እንክዋ ጄኔራል ናፒር ባዘዘው መሰረት በመቅደላ ተሰስበው የነበሩት ሁሉ ቅርሶች ለጨረታ ቀርበው ነበር በማለት ለማስመሰል ተሞከረ እንጂ አንዳንድ ባለሀብቶች በተለይም ሲቪሎችና ኦፍሰሮች ራሱ ጄኔራል ናፒር ሳይቀር ቀደም ብሎው ጨረታው በይፋ ከመጀመሩ በፊት ለየራሳቸው ያከማቿቸው ቅርሶች በብዛት እንደነበሩ ድርጊቱ ካለፈ በኋላ ሊታወቅ ችሏል። ለምሳሌ ለጨረታው ካልቀረቡት ቅርሶች መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶች፣ የክብር እና የማዕረግ ልብሶቻቸው፣ በሺ የሚቆጠሩ በብራና መፅሃፍቶችና የቴዎድሮስ ማህተም፣ የአቡነ ሰላማ የወርቅ አክሊል፣ በብር ያሸበረቀ ጋሻ፣ በክብረ በዓል ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል የቴዎድሮስ ከበሮና የመሳሰሉት ከሌሎች ንብረቶች ጋር ከመቅደላ ቤተ ክርስቲያን አጥር ግቢ በነበሩት ጎጆዎች ውስጥ ታምቀው እንደነበር ይነገራል።

  እንደዚሁም ጨረታው ላይ ቅርሶቻቸውን ካላቀረቡት መካከል ጨዋ መስለው የሚታዩ፤ በእድሜ በሰል ያሉና የተከበሩ፣ ቀደም ሲልም የአፄ ቴዎድሮስ እስረኞች በመሆን እስር ቤት የማቀቁ ወንጌል ሰባኪዎች የነበሩ አውሮፓውያን ገና ወታደሮቹ በቡድን እየሆኑ ለዘረፋ ከመሰማራታቸው በፊት ሰርቀው ያስቀመጧቸው ቅርሶች ከእግሮቻቸው አጠገብ ተከምሮ ይታይ እንደነበር እስታሊን አብራርቶ ገልፆታል። በተለይም ከአቡኑ መቃብር ላይ ተፈፅሞ የነበረውን የስርቆት ወንጀል አስመልክቶ ሲናገር "በጣም ከሚያስገርመውና ከሚያሳዝነው ነገር ሁሉ ከእስረኞቹ መካከል አንዱ ከስድስት ወር በፊት ተቀብረው የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መቃብር ድረስ በመሄድ መቃብሩን አውጥቶና ሰብሮ ብዙ ሺ ዶላር ሊያወጣ የሚችል ከአልማዝ የተሰራ መስቀላቸውን ከአንገታቸው ላይ መንጭቆ መውሰዱ የቱን ያህል የተረገመ ሰይጣን እንደነበር ነው።" ሲል በዝርዝር አስቀምጧል።

  ቀደም ሲል ለጨርታ ያልቀረቡ የቤተመንግስት ንብረቶችና የጦር መሳሪያዎች ተቀምጠው ከነበሩበት ከመቅደላ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን አጥር ግቢ ከሚገኙት ጎጆዎች ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስን የማዕረግ ልብስና ዘውዶቻቸውን፣ መፅሃፍታቸውን፣ ፅዋቸውንና ከበሯቸውን እንደዚሁም ማኅተማቸውን ወደሀገሩ ለመውሰድ ለይቶ በመውጣት፣ የቀረውን ንብረት የወሎ ባላባት ልጅ ለነበሩት ለወይዘሮ መስተዋትና ለወጣቱ ለጃቸው ለይማም አምዴ ካስረከበ በኋላ ሶስት ሺ ቤቶች የሰፈሩበትን የመቅደላ መንደር አፄ ቴዎድሮስ የተቀበሩበት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሳይቀር በእሳት በማጋየት መቅደላን እንዳልነበረች አደረጓት።

  ይህንን ጦርነት በማስተባበር የተሳካ ውጤት ላስገኙት የቴዎድሮስን ከበሮ ሶስት የተለያዩ ብርጌዶች ከሸለሟቸው በኋላ፤ ሌሎቹን ቅርሶች አግበስብሶ ወደ አገሩ ተመለሰ።

  ምንም እንኳ ጦርነቱ እንዳበቃ የእንግሊዝ ወታደሮች ብዙ ሳይቆዩ ወደ አገራቸው የተመለሱ ቢሆንም ለመንገዳቸው ከሚገለገሉባቸው ምግብና የቤት ቁሳቁሶች ባሻገር እግረመንገዳቸውን የሚያስፈልጋቸውን ያህል ቅርሶቻችንን ከሀገር ለማስወጣት ሲሞክሩ በጉዟቸው ላይ ሳሉ አያሌ መከራ እና ስቃይ ደርሶባቸው እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል። ለምሳሌ:- ጄኔራል ናፒር በሱ የሚመሩት የጦር መኮንኖቹ እ.ኤ.ዓ. ሜይ 29 ቀን 1868 ከኢትዮጵያ ክልል ጠቅልለው ለመውጣት ወደ ሰንአፌ አካባቢ እስከተቃረቡ ድረስ ሽፍቶች አልፎ አልፎ አደጋ ይጥሉባቸው ነበር። በየጊዜያቱ የሚጥለውም ዝናብ ጉዟቸውን እንዲሰናከል አድርጎባቸዋል። በተለይም አንድ ቀን የጣለው ኃይለኛ ዝናብ መንገዳቸውን ሊዘጋባቸው ከመቻሉም በላይ የማያቋርጥ ጎርፍ ስለነበር ብዙ እንስሳትና የሰባት ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ ችሏል።

  ታሪኩ በዚህ ብቻ አላበቃም። የመቅደላን ጦርነት እስከ መጨረሻው ድረስ ሲከታተል የነበረው ጋዜጠኛ በጉዞው ላይ አጋጥሞት የነበረው ስቃይ በቀላሉ የሚገመት አልነበረም። ይህ ግለሰብ በጨረታ የሰበሰባቸውን ቅርሶች በአምስት አጋሰስ ጭኖ ከመቅደላ ወደ ሰንዓፌ ከዚያም ወደ ዙላ በሚጓዙበት ወቅት እጅግ በጣም የማያቁዓርጥ ኃይለኛ ዝናብ በመዝነቡ የተነሳ ከየተራሮቹ የሚወርደው ጎርፍ ወደ ጅረትነት፤ ከዚያም ወደ ወንዝነት እየተቀየረ በመምጣቱና የወንዙም ሙላት ጊዜ በማይሰጥ ሁኔታ እየጨመረ በመሄዱ ጋዜጠኛውና ጓደኞቹ ተስፋ ቆርጠው ካለቀላቸው በኋላ ድንገት የዝናቡ መጠን በመቀነሱ ሕይወታቸው ሊተርፍ ችሏል።

  ስለሆነም በዝናቡ ኃይል እየተሸገሸገ ወደ ወንዙ የገባው የአፈር ደለል ከፍታ፤ እስከ አንድ ሜትር በመድረሱ አጋሰሶቹ ከተጫኑት የቅርስ ሸክም ጋር ይህንን ደለል ለማቋረጥ ባለመቻላቸው ጋዜጠኛውና ጓደኞቹ ያለውዴታቸውና ያለፍላጎታቸው ክብደት ለመቀነስ ሲሉ ብቻ ከበድ ያሉትን ቅርሶች እያወጡ ጥለዋቸዋል። ከነዚህም መካከል በደላንታ ጨረታ ላይ በሃምሳ ሩፒ (የህንድ ገንዘብ) ገዝቶ ያኖረው ዘጠና ኪሎ ክብደት ይመዝን የነበረው የቴዎድሮስ ስጋጃ ይገኝበታል።

  በመጨረሻም ጋዜጠኛው ይህንን ሁሉ ፈተናና ስቃይ አልፎ ዙላ ከምትባለው የቀይ ባህራችንን ጠረፍ ደረሰ። ከዚያም በአምስት በቅሎዎች ላይ ጭነዋቸው ያመጧቸውን ቅርሶች በሳጥን አስገብቶ ካሸጋቸው በኋላ እንስሳቱን ሸጧቸው በማግስቱ "ትራንስፖርት እስቲመር ኢንጂን" ተብላ በምትጠራው አነስተኛ መርከብ እሱና የአፄ ቴዎድሮስን አራት ዘውዶች ለንግስት ቪክቶሪያ እንዲያደርስ ከተወከለው ከኮሎኔል ሚልወርድ ጋር በመሆን በስዊዝ ካናል በኩል አድርገው ጉዟቸውን ወደ እንግሊዝ አገር ጀመሩ።

  የአቡነ ሰላማን ከወርቅ የተሰራ አክሊልና የቁርባን ፅዋ ከአንድ ጦር ሜዳ ላይ ከዋለ ወታደር የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሆልምስ በአራት የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ ገዝቶት እንደነበር ቀደም ስል ተጠቅሷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግሊዞች ድል አገኘን ብለው ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የተጠቀሱትን ሁሉት ቅርሶች ሪቻርድ ሆልምስ ከኮሎኔል ፍሬዘር፤ ከኮሎኔል ሚልወርድና ከኮሎኔል ካሜሩን ጋር በመመሳጠር "ዘ አቢስንያን ፕራይዝ ፈንድ ኮሚቴ" በሚል ስም ለብሪትሽ ሙዚየም በሁለት ሺ የእንግሊዝ ፓውንድ እንዲሸጥላቸው እ.ኤ.ዓ. ጁላይ 1/1868 አቅርበውት እንደነበር የደብዳቤ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

  በሽያጭም ሆነ ወይም በስጦታ መተላለፋቸው ለጊዜው ባይታወቅም ባሁኑ ጊዜ ከመቅደላ የተወሰዱት ቅርሶች በእንግሊዝ አገር ሙዚየሞች ውስጥ ባመጧቸው ሰዎች ስም ተመዝግበው ይገኛሉ። ለምሳሌ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ በፃፈው "ዘ ፕሬስተር ጆን" ተብሎ በሚጠራው መፅሐፍ መጨረሻ ላይ ተርጓሚዎቹና አዘጋጆቹ ሃንቲንግፎርድና ቤክንግሃም እንደጠቀሱት በብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ "ሆልምስ ኮሌክሽን" እየተባሉ የሚጠሩ አስር ታቦቶች ከመኖራቸውም በላይ ብዛታቸው ከአንድ ሺህ በላይ የሚደርስ የኢትዮጵያ የእጅ ፅሁፍ መፅሀፎች በተጠቀሰው ሙዚየም ውስጥ ተደርድረው ለሕዝብ ይታያሉ።

  ባጠቃላይ፣ የሀገሪቱ ሀብቶች በተለያዩ ስፍራዎች ሙዚየሞች ውስጥ በግለሰቦችም እጅ ጭምር የሚገኙ መሆናቸው መታወቅ አለበት። ይህ ሁኔታ የተጠቃለለ ኢንቬንተሪ ለመስራት አስቸጋሪ ያደርገዋል።

  Source:
  Kasa and Kasa 
  Papers on Lives, Times and Images of Tewodros II and Yohannes IV (Institute of Ethiopian studies፣ Addis Ababa University)
  This specific paper by Girma Kidane
 • loader Loading content ...
 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  የመጨረሻው የመቅደላ ግብግብ ሰኞ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ወደማቆሙ ተቃረበ:: የእንግሊዝ ጦር ሰራዊት ቴዎድሮስን አድኖ ለመያዝ በያቅጣጫው መሯሯጥ ጀመረ:: የቴዎድሮስን ሁኔታ አስመልክቶ የኒውዮርክ ታይምስ ሪፖርተር እስታንሊ ሲናገር ሰኞ ከቀኑ አስር ሰዓት አካባቢ እንግሊዝ በመቅደላ ላይ ካሰማራቻቸው ወታደሮች መካከል ሁለት የአይሪሽ ወታደሮች የተኩስ ድምፅ ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተክለፈለፉ እንደደረሱ; አንድ ያልታወቀ ኢትዮጵያው ከመሬት ላይ ተዘርሮ ለመሞት በማጣጣር ላይ እንዳለ ያገኙታል:: የግለሰቡ ጣር ስሜት ሳይሰጣቸው ቀድሞውንም ከኛ የተሰረቀ ነው በማለት በቀኝ እጁ አቅጣጫ የወደቀውን ሽጉጥ አንስተው ይወስዱበታል:: ይህ አልበቃ ብሏቸው የጣቱን የወርቅ ቀለበት እና የአንገቱን የወርቅ መስቀል ይዘርፉታል:: ከዚያም የወሰዱትን ሽጉጥ እያገላበጡ በማድነቅ ሲመለከቱ ከጎን በኩል ከብር ተቀርፆ የተለበደ ፅሁፍ ያገኙበታል:: ፅሁፉም "እንደ ኤ.አ. 1854 ለአሽከሬ ለፕላውዲን የአቢሲንያው ንጉስ ቴዎድሮስ ላደረጉለት ቅንነት የተመላበት ደግነት ያለኝን አድናቆት ለመግለፅ ከታላቁዓ ብሪታንያና የአየርላንድ ንግስት ቪክቶሪያ የተላከ ስጦታ" የሚል ነበር::

  ወታደሮቹ ፅሁፉን ካነበቡ በህዋላ ከነከናቸው:: አንደኛው ወታደር "ቴዎድሮስ ይሆን እንዴ?" በማለት ነፍሱ ልትወጣ የተቃረበውን ግለሰብ ማስተዋል ጀመረ::ምናልባትም ወታደሮቹ ሊለዩዋቸው ያልቻሉበት ሌላው ምክንያት አፄ ቴዎድሮስ በጠላት መወረራቸውን እንደተረዱ ከቤተሰቦቻቸው እና ከቅርብ ተከታዮቻቸው ጋር ተሰናብተው በሽጉጥ እራሳቸውን መተው እንደወደቁ ጠላቶቻቸው እሳቸው መሆናቸውን እንዳይለዩዋቸው በማሰብ ወልደ ጋብር የሚባለው የቤት አሽከራቸው የሚደርቧትን ባለቀጭን ጥለት ነጠላቸውንና ታጥቀውት የነበረውን ባለከፋይ ቀበቷቸውን አውልቆ በመውሰድ ቁጥራቸው አስራ አምስት ያህል ከሚሆን ከቴዎድሮስ ጭፍሮች ጋር በማምለጥ ተሸሽጎ እንደነበር ለእንግሊዝ ኦፊሰሮች በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ ተጠቅሷል:: ሌላው ቴዎድሮስ መሆናቸው ያልታወቀበት ምክንያት አለባበሳቸው ተራ ኢትዮጵያዊ ከሚለብሰው ልብስ የተለየ ባለመሆኑ ነበር:: በተለይም ባዶ እግራቸውን ያለጫማ መታየታቸው ብቻ ሳይሆን; ከደረታቸው ስፋትና ከትከሻቸው ትልቅነት በስተቀር ቁመታቸው መካከለኛ እንጂ ረዥምና ግዙፍ ባለመሆኑ, እኒያ በሀገራቸው ላይ ተነስተውባቸው የነበሩትን ሽፍቶች ከመደምሰስ አልፈው ተርፈው በጄኔራል ናፒር የሚመራውን ዘመናዊ የእንግሊዝ ጦር እጄን አልሰጥም በማለት በድንገት የወደቁ ታላቅ አንበሳ መሆናቸውን ከቶውንም ለማመን አልቻሉም ነበር::

  ይህ በእንዲህ እንዳለ መቅደላ በእንግሊዝ ጦር ሰራዊት ቁጥጥር ስር ሆነች:: ቀደም ሲል የቴዎድሮስ እስረኞች የነበሩትም ኢትዮጵያውያን በግርግር የታሰሩበትን ቤት በመስበር የእግር ብረታቸውን መሬት እየጎተቱ በአደባባይ መታየት ጀመሩ:: ከፊሉም እንግሊዞች ወደሰፈሩበት ካምፕ በመሄድ ተቀላቀሉ::

  ወዲያውኑ አንድ ግለሰብ እየሮጠ ሄዶ የጄኔራል ናፒር የቅርብ ረዳት ለነበረው ለሰር ቻርልስ እስቴቨሊ "እዚያ አንድ ግለሰብ ተዘርሯል; ሰዎች ቴዎድሮስ ነው ይላሉ::" በማለት ሪፖርት ያቀርባል:: እስቴቨሊ ግን በነገሩ ሙሉ በሙሉ አላመነበትም ነበር:: በዚህም ምክንያት ይህ ማንነቱ ያልታወቀውን ሬሳ በቃሬዛ ላይ በማድረግ አምጥቶ ለማሳየት በማሰብ ግለሰቡ ሬሳው ወደ ነበረበት ስፍራ ተመልሶ ሄደ:: ጭካኔ በተመላበት አኩዓሁዋን ሁለት እግሮቻቸውን በመጎተት ለቃሬዛ መሸከሚያ ተብሎ ከተሰራ የእንጨት ርብራብ ላይ እንደጣሏቸው ሶስት ጊዜ ካቃሰቱ በህዋላ ሕይወታቸው ልታልፍ ችላለች:: ይህንን ድርጊት አስመልክቶ ማርክሃም ሲያብራራ ወታደሮቹ የአፄ ቴዎድሮስን ቃሬዛ ተሸክመው ለሰር ቻርልስ ለማሳየት እንደደረሱ ታስረው የተፈቱት እስረኞች በሽቀዳደም መጀመሪያ መልካቸውን አተኩረው ካዩ በህዋላ አንድ ነገር ትዝ አላቸውና የግራ እጃቸውን ከፍ አድርገው ጣታቸውን ማየት እንደጀመሩ አንደኛው ጣታቸው ሰባራ ሆኖ አገኙት:: አፄ ቴዎድሮስ ገና በወጣትነታቸው ዘመን ጎጃም ላይ በጥይት ጣታቸው ላይ ተመተው ስለነበር የተቆረጠውን ጣት ስላዩ, ቴዎድሮስ መሆናቸውን አረጋገጡ:: ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሬሳው የአፄ ቴዎድሮስ ስለመሆኑ የቀረበው ማስረጃ በእንግሊዝ የጦር መኮንኖች ዘንድ አጠራጣሪ ስለመሰለ አፄ ቴዎድሮስ በሕይወት ሳሉ የሚያውቃቸው የነበረው ራሳም መጥቶ እንዲያያቸው ተደረገ:: ብዙ ሳይቆይ ራሳም ወዲያው እየሮጠ መቶ ሲያያቸው አፄ ቴዎድሮስ ሆነው አገኛቸው:: ምንም እንክዋን በሱና በአፄ ቴዎድሮስ መካከል አልፎ አልፎ አለመግባባት ቢፈጠርም ቆራጥ መሪ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ሁኔታውን እንደተመለከተ መንፈሱ ተረበሸ:: በተለይም ከመሞታቸው በፊት የተናገሩት ቃል ትዝ አለው:: ይሄውም "አንድ ቀን እኔ ስሞት ታየኝ ይሆናል; ከዚያም በሬሳዬ ላይ ቆመህ ይህን ደካማ ሰው በመቅበር ፋንታ ከሜዳው ላይ እንደወደቀ በስብሶ መቅረት አለበት በማለት ትረግመኝ ይሆናል" ብለው የተናገሩት ትዝ እያለው በሃዘን ተውጦ ይታይ ነበር::

  የአፄ ቴዎድሮስ መሞት በይፋ እንደታወቀ የእንግሊዝ ወታደሮች ደስታ በተመላበት ሁኔታ ባንዲራቸውን በማውለብለብ በመቅደላ ተራራ ላይ ጩሃታቸውን አስተጋቡት:: ብሔራዊ መዝሙራቸውንም አሰሙ::በቴዎድሮስ እጅ ታስረው የነበሩትም እስረኞች ሟቹ ሬሳ አካባቢ የፈንጠዝያ ግብዣ ለማድረግ ከያሉበት ተጠራሩ:: ሕዝቡም ሬሳውን በደምብ ለማየት እንዲችል ወደ ሜዳ ተጎትቶ ተቀመጠ:: ዙሪያውንም በመክበብ እርቃነ ስጋቸው እስኪታይ ድረስ የለበሱትን ልብስ በብዙ ቦታ ተለተሉት::

  በወቅቱ የአይን ምስክር በመሆን ያረጋገጠው አሜሪካዊ ሪፖርተር ሕይወታቸው ስላለፈችው የመቅደላ ጀግና ሲያብራራ "የተለየ ክብር ሳይደረግላቸው; ጠባቂ ዘብ በአጠገባቸው ሳይቆም በቃሬዛ ላይ ለብዙ ሰዓት ያህል ከመሬት ተዘርረው; ፀጉራቸው ተሸልቶ ልብሳቸው ተገፎ እና ተቀዳዶ ከፊል እርቃነ ሥጋቸውን በማየቴ የቀድሞው ቴዎድሮስ መሆናቸው አጠራጠረኝ" ይልና, "ራቅ ብዬ ስመለከት ብዙ ኦፊሰሮች በደም የተበከለውን የቴዎድሮስን ሸሚዝ ለኔ ይገባኛል በማለት ሲሟገቱ እና ሲጣሉ ተመልክቼ ነበር::" ብሎ ንግግሩን ይደመድማል::

  ስለሆነም በዚያን ጊዜ ቴዎድሮስ ሲነግሱ ለብሰውት የነበረው የክብር ልብስና በአንፃሩ ደግሞ ከሞቱ በህዋላ የተወሰደባቸው በደም የተበከለ ሸሚዝ በእንግሊዝ አገር ራቅ ባለ ሰሜናዊ ክፍል ባንክ ፊልድ ሙዚየም ተብሎ በሚጠራው መዘክር ውስጥ ሲገኝ የተሸለተው ፀጉራቸው ግን ለንደን ከተማ ናሽናል ዋር ሙዚየም ውስጥ እንግሊዞች አጉል ጀብደኝነታቸውን ለማስታወስ ብለው አስቀምጠውታል::

  ይህንን አስነዋሪ ድርጊት ያስተዋለ አንድ ታዛቢ የቴዎድሮስ ሬሳ ከፊል እርቃኑን ስለነበረ የሰው መሳቂያ ሆኗል በማለት ለናፒር ተናገረ:: ናፒር ግን የተሰራው ሥራ አንድ ወታደር ከሚያደርገው የዲስፕልን ስነስርዓት ውጪ መሆኑን እየተገነዘበ አንዳችም የቅጣት እርምጃ ሳይወስድ ቃሬዛው እንዲለብስና በማግስቱ ለቀብር እንዲዘጋጅ የሚል ትዕዛዝ ሰጠ:: ሆኖም ይህ ከመፈፀሙ በፊት በስዕል መልክ ፎቶግራፍ እንዲነሱ ተደረገ:: ከመጣበት ተልዕኮ ሌላ በስዕል በመሳል ልዩ ሙያ የነበረው የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሪቻርድ ሆምስ በደረቅ አርሳስና ብሩሽ አማካኝነት ስሎ አቀረበ:: የሳለውም ስዕል ትክክለኛውን የቴዎድሮስ መልክ የያዘ እንደነበረ የቴዎድሮስን አሟሟት ለመመርመር ከተገኘው ሐኪምና በሚስተር ራሳም ተረጋገጠ:: ከዚያም በህዋላ ቀደም ሲል ጠቅላይ የጦር አዛዤ እንዳዘዘው ሁሉ በሚስተር ራሳም አማካይነት ቃሬዛው ከስፍራው ተነስቶ የእንግሊዝ እስረኞች ይኖሩበት ከነበረው ግቢ ፒትሮ ተብላ ከምትጠራው ጎጆ ውስጥ ለቀብር እንዲዘጋጅ ተደረገ::

  የቀብሩ ስነ ስርዓት ከመፈፀሙ በፊት ስለአሟሟታቸው በሃኪሞች የተደገፈ ማስረጃ ማግኘት ያስፈልግ ስለነበረ ዶ/ር ብላንክና የአፄ ቴዎድሮስ የንስሐ አባት በተገኙበት ዶ/ር ለምስዳይን አስከሬኑን መርምረው ያገኙት ውጤት "በጥይት የተመታ ቁስል ከበስተህዋላ በኩል ጭንቅላታቸው ላይ ሲታይ; እንዲሁ ከአፋቸው ውስጥ ጠቆር ብሎ ጉድጉድ ያለ ቁስል ይታይበት እንደነበረ; የሽጉጣቸውን አፈሙዝ ከአፋቸው አጉርሰው የተኮሱት ጥይት በአፋቸው ጣራ በኩል አድርጋ የሁዋላ ጭንቅላታቸውን አልፋ የወጣች በመሆኗ ንጉሡ ራሳቸውን በራሳቸው እንደገደሉ የሚመሰክር ነው በማለት አረጋገጡ::" የምርመራው ውጤት ካበቃ በህዋላ ዶ/ር ሄንሪ ብላንክ እንዲህ ብለው ተናገሩ:: "ስሜቴን በጣም የሟቹ የቴዎድሮስ ሬሳ ነበር:: የቴዎድሮስ ሬሳ ፈገግ ብሎ ይታያል; የዚህ አይነቱን ደስታ የተመላበት ከአፄ ቴዎድሮስ በቅርብ ጊዜ በሕይወት እያሉ አይታይባቸውም ነበር:: ይህም ሁኔታ ፀጥታ የተመላበት ብዙ አስደናቂ ስራዎችን ያከናወኑ; ታላቅነትና ጨካኝነታቸውም በታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለውን የሰው ቅርፅ የያዘ በሕይወታቸው ማለፊያ ጊዜ የወጣትነታቸውን ወራት, በጀግንነት ያደርጉዋቸውን ውጊያዎች አሁንም ራሳቸውን በራሳቸው መግደላቸውን አስበው መደሰታቸውን ያሳያል::"

  ምንም እንኯ ጄኔራል ናፒር የአፄ ቴዎድሮስን ሬሳ ለቀብር እንዲዘጋጅ ብሎ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም የት ቦታና በእንዴት ያለ ሁኔታ ቀብሩ እንደሚከናወን ገና አልተወሰነም ነበር:: ይህም ጉዳይ ለሟች ባለቤት ለእቴጌ ጥሩቀርቅ በጥያቄ መልክ ቀርቦላቸው ሲመልሱ "በግል ቤተክርስቲያናቸው ውስጥ ፍትሃተ ፀሎት እንዲደረግላቸው ይፈቀድ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ" በማለት የተናገሩት በጄኔራል ናፒር ተቀባይነት በማግኘት የአፄ ቴዎድሮስ ሬሳ በጎጆው ውስጥ እንዳለ በነጭ ጨርቅ እንዲጠቀለል ተደረገ:: ከዚያም በወርቀ ዘቦ ያሸበረቀ የሀገር ልብስ ከለበሰ በህዋላ በአልጋ ላይ ተደርጎ ወደ ቀብር አመራ:: የአፄ ቴዎድሮስ የውስጥ ጠላቶች አደጋ ሊያደርጉባቸው ይችላሉ በሚል ስጋት ባለቤታቸው እቴጌ ጥሩወርቅና ልጃቸው ደጃዝማች አለማየሁ በቀብሩ ስነ ስርዓት ላይ አልተገኙም ነበር:: ይሁን እንጂ የቅርብ ዘመዶቻቸውና ጥቂት መኮንኖች በተገኙበት በሕይወታቸው ሳሉ መቅደላ ላይ አሰርተውት በነበረው በመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ስርዓተ ፀሎት ተደርጎላቸው ከአቡነ ሰላማ መቃብር አጠገብ በተወለዱ በሃምሳ አመታቸው ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. የቀብር ስነ ስርዓታቸው ተፈፀመ::

  ምንጭ:
  Kasa and Kasa 
  Papers on Lives, Times and Images of Tewodros II and Yohannes IV (Institute of Ethiopian studies, Addis Ababa University)
  Girma Kidane
 • loader Loading content ...
 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ቁጥራቸው ወደ ፲፩ የሚደርሱ የፅሁፍ ቅርሶችን ለአለም በዩኔስኮ በኩል አስመዝግባለች። እነዚህ ቅርሶች የሚከተሉት ናቸው።
  • የአርባዕቱ ወንጌል : የሃዲስ ኪዳን ድፍል የሆኑትን የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስ እና የዮሃንስ ወንጌልን የያዘ መፅሃፍ ነው። 29.5x20.5 ሴ.ሜ . መጠን ያለው ባለ 554 ገፅ ብራና መፅሃፍ ነው።
  • የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት : የሃዲስ ኪዳን ክፍት የሆኑትን 14ቱን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት የያዘ መፅሐፍ ነው። 34.6x25 ሴ.ሜ . መጠን ያለው ባለ 281 ገፅ ብራና መፅሃፍ ነው።
  • መዝሙረ ዳዊት : መቶ ሃምሳ መዝሙራትን የያዘ፤ ኣብዛኛውን በእስራኤሉ ንጉስ ዳዊት እንደተደረሰ የሚታመን እና በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምእመናን ለፀሎት የሚገለገሉበት፣ የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ደግሞ ንባብን ለመለማመድ የሚጠቀሙበት መፅሃፍ ነው።
  • ግብረ ህማማት : በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሞነ ህማማት የሚነበብ ከብሉይ፣ ከሃዲስ እና ከሊቃውንት ትምህርቶች የተውጣጡ ንባባትን የያዘ ትልቅ መፅሃፍ ነው። 40x33.5 ሴ.ሜ . መጠን ያለው ባለ 434 ገፅ የብራና መፅሐፍ ነው።
  • መፅሃፈ ሄኖክ : ሄኖክ የአዳም የልጅ ልጅ ከሆኑት የመፅሃፍ ቅዱስ አበው አንዱ ሲሆን መፅሃፉም ከተፃፈበት ዘመን ጀምሮ እስከ አለም ፍፃሜ በዚህ አለም ላይ ስለሚሆነው ማናቸውም ነገር የሚናገር የትንቢት መፅሃፍ ነው። ይህ መፅሃፍ በሌሎች አለማት ጠፍቶ በኢትዮጵያ መገኘቱ ይታወቃል። 15.5x19 ሴ.ሜ. መጠንና 160 የብራና ቅጠሎች የያዘ መፅሃፍ ነው።
  • መፅሃፈ ቅዳሴ : የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምትጠቀምባቸው 14tቱን ቅዳሴዎች አጠቃሎ የያዘ መፅሃፍ ነው። 195x155 ሴ.ሜ. መጠንና 78 የብራና ቅጠሎች የያዘ መፅሃፍ ነው።
  • የዳግማዊ ምኒሊክ ታሪክ (ታሪከ ነገስት ዘዳግማዊ ምኒልክ) : ይህ መፅሃፍ በንጉሱ ዘመን በነበሩት በፀሃፌ ትእዛዝ ገብረ ስላሴ ወልደ አረጋይ በአማርኛ የተፃፈ የዳግማዊ ምኒልክ ታሪክ ነው። 21x17 ሴ.ሜ. መጠንና 178 ገፆች ያሉት መፅሃፍ ነው።
  • ፍትሃ ነገስት : ከ14ኛው መካከለኛ ክፍለ ዘመን እስከ 1923 ዓ/ም ድረስ ኢትዮጵያውያን ሲተዳደሩበት የነበረ ስጋዊ እና መንፈሳዊ ጉዳዮችን የያዘ የህግ መፅሃፍ ነው። 22x23 ሴ.ሜ. መጠንና 146 ገፆች ያሉት መፅሃፍ ነው።
  • ታሪከ ነገስት : የመፅሃፉ ይዘት ባብዛኛው ስለ አመተ አለም ዐቆጣጠር፣ ስለ ኢትዮጵያ ነገስታት እንዲሁም በአራተኛው እና በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኒቂያ፣ በኤፌሶን፣ በቁስጥንጥኒያ እና በኬልቄዶን ስለተደረጉ የሃይማኖት ጉባኤዎች እና ክርክሮች የሚያስረዳ ነው። 21.3x16.5 ሴ.ሜ. መጠን አለው።
  • ዓጼ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ንግስት ቪክቶሪያ የፃፉት ደብዳቤ : ደብዳቤው የቱርኮችን ጥቃት ለመቇቇም፣ እንግሊዝን እርዳታ ስለመሻት የተፃፈ ነው።
  • ዳግማዊ ምኒልክ ለመስኮብ ቄሳር ዳግማዊ ኒኮላስ የፃፉት ደብዳቤ : ደብዳቤው በ1888 ዓ.ም.  ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ጣልያኖችን ድል ማድረጋቸውና የሩስያ ቀይ መስቀል ማህበር ከኢትዮጵያ ወገን በመቆሙ ምስጋና የቀረበበት ነው። በተጨማሪም የመስኮብ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር የንጉሱን ጥያቄ የያዘ ደብዳቤ ነው።

  ምንጭ:
  ህብረ ኢትዮጵያ
  በቴዎድሮስ በየነ
 • loader Loading content ...
 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  ለወጣቱ የምኒልክ አልጋ ወራሽ ለልጅ እያሱ ምክር ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያን በልማት ጎዳና ለመውሰድ አስፈላጊ ናቸው ያሏቸውን እርምጃዎች በሚከተለው መልክ አስቀምጠው ነበር።


                   ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ።

  • አንደኛ:
  ለመንግስት የሚሆን ገንዘብ እና ለንጉሡ የሚሆን ገንዘብ ይለይ። ሹማምንቱ በደሞዝ ይደሩ። ካገር የሚወጣውም ግብር ለመንግስት ይግባ። የጦርም ሰራዊት ሁሉ የንጉሡ ይሁን። ያገር ምስለኔና የጦር አለቃ በያገሩ ይለይ። መጀመሪያው ባላገሩን የሚያዝ ሁለተኛው ግን ወታደሮቹን።

  የንጉሱና የመንግስት ገንዘብ የተባለው ትርጉሙ እንዲህ ነው። የንጉሥ ገንዘብ ማለት ያ ለግብር እና ለሌላ የንጉሡ ቤት ጉዳይ የሚያስፈልግ ገንዘብ ነው። የመንግስት ገንዘብ ማለት ግን ያ ለሠራዊት ደሞዝ፣ ለመንገዶች እና ለትምህርት ቤቶች ማሰሪያ የጦር መሣሪያዎችም መግዣ ለሌላ እንዲህ የመሰለውም የውጭ ጉዳይ የሚሆነው ገንዘብ ነው።

  • ሁለተኛ:
  ህዝቡ ለመንግስት የሚከፍለው ግብር እንደየሃብቱ መጠን ቁርጥ ሆኖ ይታወቅለት። የሕዝቡም ቁጥር በመዝገብ ይግባ። እንዲሁም በየዓመት የሚወለደውና የሚሞተውም የሚጋባውና የሚፋታውም በመዝገብ ይታወቅ።

  • ሶስተኛ:
  ሕዝቡም የሚከፍለው ግብር በብር እንጅ በእህል በማርም በፍሪዳም አይሁን። የመንግስት ሥራ ሁሉም በባላገር አይሠራ፤ በባለ ደሞዝ እንጅ። ባላገሩም የሚከፍለው ግብር በመላው አገር እኩል አይሁን፤ ያውራጃው ሀብት እየታየ እንጅ። አሁን ቤጌምድር፣ ሰሜን ላስታ፣ ጎጃም፣ የጁ፣ ወሎ ብዙ ብር አይገኝበትም፤ ስለዚህ እንደሃብታሞቹ ሸዋና ትግሬ ሊገብሩ አይቻላቸውም።

  • አራተኛ:
  ያማርኛ ቇንቇ ገና ሰዋስው አልተበጀለትም። ስለዚህ መንግስታችን ከያገሩ ስዋስው የሚያውቁትን ሊቃውንት ሰብስቦ የአማርኛ ቇንቇን ስዋስው ቢያስወጣ ደግ ነው። በያገሩ አውራ ከተማ እንደ አውሮጳ ስርዓት ያበሻን ፊደልና ያማርኛን ቇንቇ ማስተማሪያ ቤቶች ይከፈቱ። ባዲስ አበባ፣ በሐረርጌ፣ በጎንደር፣ በአክሱም ግን አውራ የትምህርት ቤቶች በንዲህ ያለ ስርዓት ይቁሙ። በያንዳንዱ የትምህርት ቤት አራት የኤሮጳ መምህራንና አምስት ያበሻ መምህራን ይሹሙበት። የያንዳንዱ የኤሮጳ መምህርም ሥራ እንዲህ ይሁን። አንዱ የቁጥር እና የሂሳብ አስተማሪ፣ ሁለተኛው የዓለም ታሪክና ጂኦግራፊያ አስተማሪ፣ ሶስተኛው የንግሊዝ ቇንቇ አስተማሪ፣ አራተኛው የፈረንሳዊ ቇንቇ አስተማሪ። በአክሱም ግን በአንግሊዝ ቇንቇ መምህር ፈንታ የኢጣልያ ቇንቇ አስተማሪ ቢሾም ይሻላል። ያበሾቹ መምህራን ሥራ ግን ይህ ይሁን፤ አንዱ የወንጌል አስተማሪ፣ ሁለተኛው ያማርኛን ቇንቇ አገባብ አስተማሪ፣ ሶስተኛው የመንግስታችንን ታሪክ አስተማሪ፣ አራተኛው የፍትሐ ነገስት አስተማሪ።

  ስላራቱም አውራ የትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጉን መምህራን አስራ ስድስት የኤሮጳ ሰዎችና ሃያ አበሾች ናቸው። አንድ ደልዳላ የኤሮጳ መምህርም በሁለት ሺህ ብር ባመት ይገኛል። ያበሻውም አንድ አስተማሪ ሶስት መቶ ብር ባመት ቢያገኝ ይበቃዋል። ስለዚህ ለመምህራን የሚሆነው ደሞዝ በየዓመቱ 38 ሺህ ብር ነው። ለትምህርት ቤቶችም ሌላ ጉዳይ ሁሉ 132 ሺህ ብር ይበቃል። ስለዚህ አውራዎቹ የትምህርት ቤቶች የሚያስፈልገው ኪሳራ 500 ሺህ ብር በዓመት ብቻ ነው። ፊደልን ያላጠና ልጅም በአውሮቹ የትምህርት ቤቶች አይግባ። የፊደል ማስተማሪያ ቤት ግን ያውራዎቹ ገዦች እንዲያስባቸው መንግስት የግድ ይበላችው።

  ያገራችንም ሰው ፊደልን ለመማር ቢተጋ አገራችን ቶሎ በቀናች።ፊደልንም መማር እጅግ ቀላል ነገር ነው። በሱዳን መሬት የሚኖር አንድ ትጉህ የወሎ ልጅ እድሜው 35 ዓመት እስኪሆነው ድረስ ምንም አያውቅም ኖሮ አሁን አማርኛን እና ዓረብኛን አጥርቶ ይፅፋል። ብዙዎችም ያገራችን ሰዎች የዚያን ብልህ ወሎዬ መንገድ ቢከተሉ አገራችን በተጠቀመች። ደሞም የኤሮጳን ሰራተኞች አምጥተው በአዲስ አበባ፣ በጎንደርም እንዲሁም በአክሱም የእጅ ሥራ ማስተማሪያ ቤቶች ቢበጁ ማለፊያ ነበር። መንግስትም ለንደዚህ ያለ የትምህርት ቤቶች ምንም ብዙ ዋጋ ቢያጠፋ ግድ የለም ነበር። ወዲያው የሚያስፈልገውን ሥራ በነዚያ የትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሰራ ነበርና። እንደዚህ ያለ ጠቃሚ የትምህርት ቤት በካርቱም ከተማ ተነጅቷልና መንግስታችን ወደዚያ ተመልካች ይላክ።

  • አምስተኛ:
  ፍትሃ ነገስታችን ከዛሬው ያደባባይ ስርዓት ጋር አይስማማም። ስለዚህ መንግስት የሥርዓት አዋቂዎችን ሰብስቦ ከኤሮፓ ስርዓት ጋር የተስማማ ፍትሃ ነገስት ያውጣ። ይህም ሲደረግ የኤሮጳ ስርዓትን የሚያውቅ አማካሪ ያስፈልጋል። የተፃፈ ስርዓት የሌለው መንግስት ብዙ እድሜ የለውም።

  • ስድስተኛ:
  ያገራችን ሰራዊት ስርዓት የለውም። ስለዚህ የኤሮፓን መክዋንንት አምጥተው ሰልፍን ቢማር ማለፊያ ነበር። እንዲሁም የኤሮፓን መምህራን አምጥተው ባዲስ አበባ ላይ የጦር ትምህርት ቤት ይበጅ። ላገራችን የሚስማማ ማለፊያ አይነት የጦር ትምህርት ቤትም በካርቱም ከተማ ተበጅቷል። ስለዚህ መንግስታችን ወደዚያ ተመልካች ይስደድ። የሰራውትም ብዛት በልክ ይሁን። ሰራዊት ቢበዛ መንግስት ይደሄያል እንጅ አይበረታም።

  • ሰባተኛ:
  የዛሬው የመንግሥታችን ብር የተበላሸ ነው። ስርዓት ውል የለውም። ባንዱም አውራጃ በጨው በሌላው በጥይት ይገበያያል። ስለዚህ መንግስት ለመላይ ኢትዮጵያ የሚሆን የገንዘብ ስርዓት በቶሎ ያላወጣ እንደሆነ ንግድ ሊለማ አይችልም።

  • ስምንተኛ:
  ላገራችን ነጋዴ ስርዓት እስኪወጣለት ድረስ መንግስታችን አይቀናም። በሩና ቀራጩ ብዙ ነው። ከሶስት ዓመት በፊት አንድ አደፋር የጎንደር ነጋዴ በመተማ ግመሎች እንደተወደዱ ሰምቶ ግመሎችን ሊገዛ ወደ ጥልጣል መሬት ወረደ። ገዝቶ ሲመላለስ ያገኘውንም መከራ እንዲህ ሲል አጫወተኝ። ከጥልጣል መሬት ግመሎችን ይዤ ተነስቼ መተማ እስክገባ ድረስ በረኞቹ ላይ ቀረጥ ከፈልሁ። በየበሩም ጉቦ እስኪቀበሉ ድረስ አናሳልፍም እያሉ መከራ ሲያበሉኝ ነበር። መተማም ደርሼ ግመሎቹን ብሸጥ ስላገኘሁት መከራ የሚክስ ጥቅም አላፈራሁም። በዚህ ምክንያት ይህ አይነት ንግድ እነግዳለሁ ብዬ አይደግመኝም። ያ ሰው እውነቱን ነው። የግመሎቹም ንግድ ቢቀር የሚጎዳ እርሱ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ከሁሉ ይልቅ ያገራችን መንግስት ያገራችን የቀረጥ ስርዓት ያለው ቢሆን ብዙ ግመሎች ሲሸጡ መንግስት ገንዘብ ያገኝ ነበር። ነጋዴዎቹም በሚያገኙት ትርፍ በሬና ላም ገዝተው ወይም በሌላ አይነት ሥራ አገርን ባለሙ። ግመሎቹ አርጅተው እስኪሞቱ ድረስ የጥልጣልን ሜዳ ሳር ቢበሉ ግን መንግስታችን የሚያገኘው ጥቅም ምንድን ነው?

  ባንድ መንግስት ውስጥ ብዙ በር ሊበጅ አይገባም። ለመንግሥትም ትልቅ ጉዳት ነውና። ምነው ወደ ሱዳን ወይም ወደ ሐማሴን ተመልካቾች ሰደን ስርዓት አንማርም?

  • ዘጠነኛ:
  ህዝቡ ባንድ መንግስት ውስጥ መሆኑን አጥብቆ እንዲታወቀው አገሩን የሚዞሩ ተቆጣጣሪዎች ይሹሙበት። እነሱም ባገር ግዛት ከሚንስትር በታች ይሁኑ።

  • አስረኛ:
  የሃይማኖት አርነት ይታወጅ። የሃይማኖት ጥቅም መሆኑን የማያውቅ ብዙ ሰው ይኖራል። ስለዚህ የሚከተለውን ብናስተውል ደግ ነው። ያገራችን ሰው የተዋህዶ ሃይማኖት ከሁሉ ሃይማኖት ይበልጣል ብሎ ያምናል። በልጦ ግን ምን ረባን? ማንስ አወቀው? ያገራችን ካህናት መንግስት ጠበቃቸው ሆኖ ሌላ ሃይማኖት እንዳይገባ አውቀው ሃይማኖታቸውን ለሕዝቡ ለገልፁለት ሃሳብ የላቸውም። ስለዚህ ህዝቡ እንክዋን ተዋህዶ ማለት ምንድን እንደሆነ አይለይ፤ የክርስትያን የሃይማኖት አውራ መሰረት የወንጌልን ቃል አያውቅም። ስለዚህ አጉል ቀረ፤ የሃይማኖት አርነት እስኪታወጅ ድረስም አጏጉል ይቀራል። ለዚህም ነገር ምስክር በሀማሴን እናገኛለን። በድሮ ዘመን በዚያች አገር መሃይማን ይቅርና ብዙ ቄሶች ሃይማኖታቸውን ሳያውቁ ይኖሩ ነበር። ፕሮቴስታንቶች እና ካቶሊኮች ከመጡ ወዲህ ግን ትንሹም ትልቁም የወንጌልን ቃል አውቆ በትርጉሙ ይከራከራል። ካህናቱም በል አምጣ ቢበዛባቸው ያስተምሩ ጀመር። በዚህ ምክንያት የሃይማኖት አርነት ቢታወጅ ሃይማኖት ይታወቃል እንጂ አያጠፋም።

  ደግሞም ባገራችን አንድ የድንቁርና ነገር አለ። ሃይማኖቱ ተዋህዶ ያልሆነ ሰው ሁሉ እንደ እርኩስ ይቆጠራል። ይህም እጅግ ያስቃል። አዕምሮ የሌለው ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳያውቅ የእግዚአብሔር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል።

  ሃይማኖት የልብ ነገር ነው። ስለዚህ ሰማያዊው ንጉስ እንጂ የዚህ ዓለም ንጉሥ አይቆጣጠረውም። ወንጌል የቄሳርን ለቄሳር ስጡ የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር ያለውም በዚሁ ቢተረጎም ለመንግሥታችን ሳይበጅ አይቀርም።

  ምንጭ:
  የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ስራዎች
  አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ
 • loader Loading content ...
 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  ወ/ ሮ ሙሉመቤት እምሩ ከፋሺስት ጣልያን ወረራ በፊት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን ድሬዳዋ ካጠናቀቁ በሇላ አዲስ አበባ ከሚገኘው ሊሴ ገብረማሪያም ት/ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

  በግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ መልካም ፍቃድ የበረራ ትምህርት እንዲማሩ ተፈቅዶላቸው ኮሎኔል ሮቢንሰን እና ባህሩ ካባ ታይገር ሞዝ በምትባለው አውሮፕላን እንዳስተማሯቸውና በ1928 ዓም በጣሊያን ፋሺስት ወረራ ምክንያት የበረራ ትምህርታቸውን እንዳቇረጡ ታውቇል። ወይዘሮ ሙሉመቤት በህይወት ሳሉ "መነን" ይባል ለነበረው መፅሄት በጊዜው ስለነበረው የበረራ ትምህርት ቤትና ስለ አብራሪነታቸው ቃለ መጠይቅ አርጎላቸው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።


                                   ወይዘሮ ሙሉመቤት እምሩ

  ከጠላት ወረራ በሇላ በንጉሰ ነገስቱ የበላይ ጠባቂነት ኢምፔሪያል የአየር ክበብ በመባል አዲስ አበባ ውስጥ ተቇቁሞ የነበረው ክበብ፤ ለበረራ ትምህርት በሰዓት 22.5 ብር እያስከፈለ በሚያስተምርበት ጊዜ ወ/ ሮ አሰገደች አሰፋ በዚህ እድል በመጠቀም ኮሎኔል ሮቢንሰን የበረራ ትምህርት አስተምሯቸው በ1944 ዓም ለብቻቸው ለማብረር ችለዋል።


                      ወይዘሮ አሰገደች አሰፋ

  ሁለቱ ወይዛዝርት ፓይለቶች በአንድ ወቅት ተገናኝተው ስለበረራ ታሪካቸው ሲወያዩ ወ/ ሮ ሙሉመቤት በጦርነት ምክንያት ለብቻቸው ለመብረር ሳይችሉ ትምህርታቸው መቇረጡን እንደነገሯቸው ወ/ ሮ አሰገደች ለዚህ መፅሃፍ ደራሲ አስረድተዋል። 

  ስለዚህ፣ የመጀመርያዋ በረራ ትምህርት ቤት የገቡት ኢትዮጵያዊት ወይዘሮ ሙሉመቤት እምሩ ሲሆኑ የመጀመሪያይቱ ለብቻቸው አይሮፕላን አብራሪ ለመሆን ደግሞ ወይዘሮ አሰገደች አሰፋ ናቸው።

  ምንጭ:
  አቪዬሽን በኢትዮጵያ
  ካፒቴን መኮንን በሪ
 • loader Loading content ...
 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  ቪስኮምት ጃክ ዴ ሲቦር የተባሉ የታወቁ ፈረንሳያዊ አገር ጎብኚ መለያ ቁጥሯ 884 ጃፕሲ ሞዝ በሆነው አውሮፕላን በ1928/1929 ሳፋሪ ሁለት በሚል ስያሜ አለምን ዞሯል። እነ ሙሴ አንድሬ ማዬ የኢትዮጵያን አቪዬሽን በሚያካሂዱበት ዘመን እኚህ አገር ጎብኚ ከሙሴ ማዬ ጋር ወዳጅነት ስለነበራቸው ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ የመጀመርያ አገር ጎብኚ በራሪ ለመሆን ስለፈለጉ ራስ ተፈሪን እንዲያስፈቅዱላቸው በፅሁፍ ይጠይቇቸዋል።

  የኢትዮጵያ መንግስት አልጋወራሻና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ ልዑል ተፈሪ መኮንን በኢትዮጵያ አየር ላይ ማንኛውም የውጭ ሃገር አውሮፕላን እንዳይበር ጥብቅ ትእዛዝ አስተላልፈው ስለነበር ፍቃድ ጠያቂው አገር ጎብኚ ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ በሚያደርጉት በረራ የአውሮፕላኗን ክንፍና ግራና ቀኝ የኢትዮጵያ ባንዲራ መቀባት እንዳለበት የሚገልፅ ፍቃድ ተላከላቸው። በተጨማሪም ስለሚከተሉት የበረራ መስመር ጅቡቲ እንደደረሱ እንደሚገለፅላቸው መልእክቱ ያመለክታል።

  ዴ ሲቦርና ባለቤታቸው ከሚኖሩበት ከሎንዶን ከተማ ከብረት በተሰራችው ሞዝ አውሮፕላናቸው ሳፋሪ ሶስት ብለው የሰየሙትን ጉዞ በግንቦት1922 ዓ.ም. ጀመሩ። የበረራው ፕላን ከሎንዶን - ፓሪስ - ኒስ - ትሪፖሊ - ካይሮ - ፖርትሱዳን - ጅቡቲ ስለነበር እስከ ፖርት ሱዳን የነበረው ጉዞ በሰላም ተከናውኗል። ከዚያም በጧት ሲነሱ አየር ላይ ያጋጠማቸው ነፋስ ከሇላ ስለነበር ፍጥነታቸው በመጨመሩ ተደስተው ጉዟቸውን ሲቀጥሉ ነፋሱ አቅጣጫውን ይለውጠውና ከፊት ለፊት የሚመጣ ሆኖ ጠንካራ ሆነባቸው። የነበራቸው ነዳጅ ጅቡቲ እንደማያደርሳቸው ሲያውቁ ወደ ፖርትሱዳን ተመልሰው ሲበሩ በመጀመርያ በረራቸው ያስደሰታቸው ነፋስ ተቃራኒ ሆኖ ከተነሱበት አውሮፕላን ማረፊያ ለመድረስ አለመቻላቸውን ተረዱ። ስለዚህ ባህረ ኤርትራ ዳርቻ ከምትገኘው ቶካር ከምትባለው ትንሽ መንደር ለማረፍ ተገደዱ። በማግስቱ ለመጠባበቂያ በታኒካ የያዙትን ነዳጅ ሞልተው በረራቸውን ወደ ጅቡቲ ቀጥለው በሰላም ደረሱ።

  በታዘዙት መሰረት ከጅቡቲ በረራውን ለመጀመር መዘጋጀታቸውን በቴሌግራም ያስታውቃሉ። የተላከላቸው የቴሌግራሙ መልስ ከ500 ሜትር ከፍታ በላይ እንዳያበሩ ያዝና ቢሾፍቱ አካባቢ ከሚገኘው ሃይቅ ላይ ሲደርሱ አየር ላይ ሲደርሱ አየር ላይ እየዞሩ ከሚጠብቇቸው ከሁለት ፓቴዝ አይሮፕላኖች ጋር መገናኘት እንደሚኖርባቸው ይገልፃል። ከዚያም የባቡሩን ሃዲድ በመከተል ከሁለቱ አውሮፕላኖች መሃከል ሆነው እያበረሩ አዲስ አበባ አየር ላይ ሲደርሱ መሪውን አውሮፕላን ተከትለው ሁለተኛ ሆነው እንዲያርፉ ያዛል። ወደ አዲስ አበባ ከማምራታቸው በፊት ድሬ ዳዋ አርፈው የሃረርን ከተማ ጎብኝተዋል። ጃንሜዳ እንዳረፉ ለክብራቸው ተሰልፎ የነበረውን ሰልፍ ጎብኝተዋል።

  ምንጭ:
  አቪዬሽን በኢትዮጵያ
  ካፕቴን መኮንን በሪ
 • loader Loading content ...
 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  ሳይበሉ ማግሳት እንደማይቻል ሁሉ፣ ሳይሰሩ ለመክበር መመኘትም በሃሳብ ውቅያኖስ ተውጦ እንደመቅረት ያለ ነው።

  ምንጭ:  
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  አሳ በመቃጥን እና በመረብ ሲያዝ ኣልጠግብ ባይ በእጅ ለመያዝ አለቱን በመፈንቀል ዘንዶ እንዲያወጣ፤ ሰርተው ያላገኙትን የሰው ሃብት አንጋጦ ማየትም የራስን እስከማጣት ያደርሳል።

  ምንጭ:  
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  ከእጅ የወደቀ እንቁላል መፍረጡ፣ መፍረሱ፣ እና መሰበሩ ኤንደማይጠረጠር ሁሉ፤ ከአፍ የወጣ ቃልም እሰው ጆሮ ስለሚደርስ ማስቀረት አለመቻሉን ለመግለጥ ያገለግላል።

  ምንጭ:  
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
 • @Mergia   2 years ago
  Sewasewer
  ብድር ጠያቂው ያልታመነ ወይም ንብረቱ ዝቅተኛ ቢሆንም ዋሱ አጥጋቢ ከሆነ በርሱ አማካኝነት ብድሩ ይሰጠው ማለት ነው።

  ምንጭ:  
  የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል ስብስብ ስራዎች።
 • loader Loading content ...
  Load more...
loader Loading content ...

Comments (6)


 • @Mergia   1 year ago
  Sewasewer
  እናመሰግናለን ጎሳ! "ሱሪህን ፍታና ተንጎራደድ" አሁንም ሲባል ሰምቻለሁ :) እንደዛ ማድረጉ የምር ለውጡ ምን እንደሆነ ግን እንጃ :)
 • @Mergia   1 year ago
  Sewasewer
  እናመሰግናለን መርሻ! ልብ የሚነካ ነገር ነው :(
 • @Mergia   1 year ago
  Sewasewer
  የቅዱስ ያሬድን ታሪክ እንደዚህ አጠር ባለ መልኩ ማቅረቡ ቆንጆ ነው። ከላይ ሌሎች የሰጡት አስተያየት ደግሞ እውነትንቱ ቢጣራ እና ቢስተካከል ግርም ነው እላለሁ። አመሰግናለሁ!
 • @Mergia   1 year ago
  Sewasewer
  Great question and answers! Thank you all! Such Q&A will definitely make sewasew a great place ...
 • @Mergia   1 year ago
  Sewasewer
  እውነትም :) አመሰግናለሁ!
 • @Mergia   1 year ago
  Sewasewer
  hahaha ... yeah!
loader Loading content ...