loader

Topics (4)


loader Loading content ...

Explanations (3)


 • @፩ ኢትዮጵያ   1 year ago
  Sewasewer
  በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ እየተዘወተረ ያለና በደብል ዲጂት (Double Digit) በፈጣን ሁኔታ በመስፋፋት ላይ የሚገኝ ‘ጫት’ የተሰኘ ቅጠል ስለመኖሩ ሁላችንም የምናውቀው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ብዙሃን ይህ ቅጠል ወጣቱን ትውልድ ለሱስ በመዳረግ ለከፋ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የጤና ቀውስ የሚዳርግ ስለሆነ መታገድ አልያም በሽያጭና አጠቃቀም ረገድ ጥብቅ ቁጥጥርና ህግ ሊበጅለት ይገባል ሲሉ ከፊሎች ደግሞ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ሚና ከመጫወት ባለፈ የአያሌ ህብረተሰብ ክፍሎች የህልውና መሰረት ስለሆነ እንዲህ በዋዛ ለማስቀረት የሚቻል አይደለም ይላሉ፡፡ በዚህ ቅጠል ፍቅር የወደቁ አንዳዶች እንቅልፍና ድብርትን በማባረር ነቃ ለማለት ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አንዳዶች ደግሞ ለመዝናናት፣ ጊዜ ለማሳለፍና መቃሙ የሚፈጥረውን የጨረፍታ የደስታ ስሜት ለማጣጣም ነው ጫትን የምንጠቀው በማለት ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ይህ ቅጠል ጉንፋንን፣ ተቅማጥንና ሌሎችም የህመም ስሜቶችን ለመዋጋት እንደሚጠቅምም የሚያምኑ አሉ፡፡ በዚህ ቅጠል ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ እንደውም ጫት ተጠቃሚዎቹን ለጨጓራ ህመም፣ ለበዛ የደም ግፊት፣ ለመተንፈሻ አካሎች ችግር፣ ለሆድ ድርቀት፣ ለጥርስ ማለቅ፣ ለስንፈተ ወሲብና ለእንቅልፍ ማጣት የሚዳርግ ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ ጫት በተጠቃሚውና ቤተሰቡ ዘንድ የሚፈጥረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አሉታዊ ገፅታዎች በሐረርና አሶሳ ከተሞች ባካኤዱት ጥናት ዳሰዋል፡፡ በጥናታቸውም የጫት ሱሰኝነት ጦስ ማህበራዊ ህይወትን ከማናጋት ባሻገር ለወንጀል ተግባራት በር የሚከፍት መሆኑንና በዚሁ ሱስ የተጠመዱ ሰዎችም ከቤተሰባቸውም ሆነ ከአካባቢያቸው ማህበረሰብ ጋር ያላቸው መስተጋብር ‘ዝቅተኛ’ አልያም ‘ምንም’ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር የራስወርቅ አክለው በዚህ ሱስ የተጠመዱ አንዳድ ባለሙያዎች በተመደቡበት ሥራ ላይ በተለይ ከምሳ ሰዓት በኃላ የማይገኙበት ሁኔታ እየተስፋፋ ስለመጣ በርካታ የመንግስት የሥራ ሰዓት በዋዛ ፈዛዛ እየባከነ ነው፤ በዚህም የተነሳ ህዝቡ ተገቢ የሆነውን ግልጋሎት እያገኘ ካለመሆኑም ባሻገር በመንግስት የዕለት ተዕለት ተግባር ላይም አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በተየያዘም የሱስ ተገዢ የሆኑ ባለሙያዎች በየዕለቱ የሚያስፈልጋቸውን የጫት ፍጆታ ለማሟላት የሚያወጡት ገንዘብ ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ባሻገር ሙስና ውስጥ በቀላሉ ሊዘፈቁ እንደሚችሉም ይታመናል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የዚህ ዕፅ አምራቾች፣ አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪዎች፣ መንግስት እንዲሁም ሌሎች አካላት ከሚያገኙትን ጥቅም አኳ ያ ‘እና ምን ይጠበስ’ ቢሉ ላይፈረድባቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከንግድ ሚኒስቴር በተገኘ መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ከ 2005-2007 ባሉት 3 አመታት ብቻ ከጫት የውጪ ንግድ 840 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡ በመጪዎቹ 5 አመታትም ይህ አሃዝ ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ይላል ተብሎ ይገመታል፡፡ በ 2002 ዓ.ም ደግሞ ከዘርፉ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ግብር ተሰብስቧል፡፡ በመጨረሻም እነ ኤርትራ፣ ሱዳንና ታንዛኒያ ሳይቃጠል በቅጠል ብለው ጫትን አግደዋል፡፡ እኛም በሂደት የነሱን ፈለግ ልንከተል ይገባል እላለሁ፡፡
 • loader Loading content ...
 • @፩ ኢትዮጵያ   1 year ago
  Sewasewer
  ከኢትዮጵያ በ 6282 ኪሎ ሜትር የምትርቀው ስካንዲቪያዊቷ ሃገር ኖርዌይ የሚደንቅና የሚያስገርም፣ የተመሰገነና ይበል የሚያሰኝ የታራሚዎች አያያዝ አላት፡፡ እኔም ለዚህ አባባሌ ተምሳሌት ይሆነኝ ዘንድ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበትና 250 ታራሚዎችን ወደሚይዘው አስገራሚው ሃልደን ማረሚያ ቤት እወስዳችኃለሁ፡፡  ሃልደን ማረሚያ ቤት ሰው የገደሉ፣ የደፈሩ፣ የዘረፉ፣ እፅ ያዘዋወሩ እንዲሁም በአሽሽ የናወዙ ሁሉ ከጥፋታቸው ይታረሙበታል ተብሎ በ 252 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገነባ ነው፡፡ ለሁለት አመታት ያህል በህግ፣ በሰብአዊ መብትና ስነ ምግባር ላይ አፅንኦት ሰጥተው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 190 ዘቦችን፣ 150 የጤና እንክብካቤ ሠራተኞችንና መምህራንን በጠቅላላው 340 ባልደረቦችን የያዘው ይህ ማረሚያ ቤት በሌሎች አለማት ላይ እንደሚገኙ ወህኒ ቤቶች የጭካኔ ተግባርና መልካም ያልሆነ አያያዝ ሲያልፍም የሚነካካው አይነት አይደለም፡፡ እንደውም አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎችም ሃገራት ምነው እንደዚህ አይነት ማረሚያ ቤት በኖረን እያሉ የሚቋምጡበት አይነት ነው፡፡ ለጥበብ ብቻ ከተመደበለት 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የማረሚያ ቤቱ በጀት ውስጥ ወጪ ተደርጎ አጥሩና የመፀዳጃ ቤቶቹ በሮች በሀገሪቱ የስነ ጥበብ ሰው ዶልክ አማካኝነት የስዕል አሻራ እንዲያርፍባቸው ተደርገል፡፡ በስዕል አጊጦ ለአይነ ስውራን ብሬልን ያከለው ይህ ማረሚያ ቤት የራሱ የምግብ አቅርቦት ቢኖረውም ታራሚዎች ለየት ያለ ምግብ አይናቸው ላይ ውል እያለ አላላውስ ቢላቸው አይቸገሩም፤ እዚያው ወደሚገኘው ግሮሰሪ ሱቅ ጎራ ብለው አንድ ኪሎ አጥንቱ የወጣለት ምርጥ የበሬ ስጋ በ 37 ፓውንድ፣ አትክልት፣ ቺዝ፣ እርጎ እንዲሁም የለስላሳ መጠጦችን ይሸምቱና ወደ ማብስያ ክፍላቸው ወስደው አጥበው ከትፈውና አብስለው ይመገባሉ፡፡ ይህንን ስነግራችሁ ቀበቶ እንኳ የማይገባበት ማረሚያ ቤት ከመቼ ጀምሮ ነው ታራሚ ያሻውን በቢላዋ ከትፎ በእሳት አብስሎ የሚመገበው ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እውነትም ይህ ምግባር ለማመን የሚያስቸግርና የሚደንቅ ቢሆንም በሃልደን ማረሚያ ቤት ግን የሚከወን እውነተኛ ተግባር ነው፡፡
  ከዚህም አልፎ መሳሪያ ያልታጠቁ ዘቦች ከታራሚዎች ጋር ወዲያና ወዲህ ሲሉ ልትመለከቱ ትችላላችሁ፡፡ሽጉጣችሁስ ወዴት አለ? ብሎ ለጠየቃቸው ማይክል ሙር ሽጉጥ አያስፈልገንም ታራሚዎቹን በአፋችን ማውራት ብቻ በቂ ነው መሳሪያችን አፋችን ነው ብለው መልሰውለታል፡፡ በአመት ለአንድ ታራሚ 93 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወጪ የሚያደርገው ሃልደን ማረሚያ ቤት ቤተ-መፅሃፍት፣ ስፖርት መስሪያ ጅምናዚየም፣ የእንጨት፣ የብረታ ብረት፣ የጨርቃ ጨርቅና ሴራሚክ መስሪያ ወርክሾ፣ ለእያንዳንዱ ታራሚ በነፍስ ወከፍ ፍላት ስክሪን ቴሌቭዥን፣ ማቀዝቀዣ ፍሪጅ፣ መፀዳጃ ቤት ከነመታጠቢያው ሻወር፣ ሙቀት እንዳይሰማቸው ማቀዝቀዣ ቬንቲሊተር፣ ከ 10-12 ለሚደርሱ ታራሚዎች ደግሞ ቪዲዮ ጌምን ጨምሮ ምግብ ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ያሟ ላ ማብሰያ ቤትና ሳሎን እንዲሁም በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚሰጠውን የልጅ አስተዳደግ ትምህርት በሚገባ ተምረው ላጠናቀቁ ታራሚዎች ለአንድ ቀን ከቤተሰባቸው ጋር አለማቸውን የሚቀጩበት ሁለት መኝታ ቤቶችን የያዘና ከላይ የጠቀስኩላችሁን የቤት ቁሳቁሶች በሙሉ ያሟ ላ ቤት በማረሚያ ቤት ውስጥ ይገኛል፡፡
  ከዚህም የሚልቀው ደግሞ ምርጫ ሲደርስ ታራሚዎች ድምፅ ስለሚሰጡ እጩ የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች ወደ ማረሚያ ቤት ጎራ ብለው ታራሚዎች በታደሙበት ከዛው ከማረሚያ ቤት ውስጥ የሚተላለፍ የቀጥታ የቴሌቭዥን ክርክር ያካኤዳሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ታራሚዎች እንደየችሎታቸው የሚስተናገዱበት ስቱዲዮም ይገኛል፡፡ በዚህ ስቱዲዮ ውስጥ የተሰሩ ጥዑመ ዜማዎች እንዲሁም ፕሮግራሞች እንዲያው ለይምሰል ብቻ ተሰርተው የሚቀመጡ አይደሉም፤ አካባቢው ላይ በሚገኝ የሬድዮ ጣቢያ በወሩ እንዲተላለፉ ይደረጋል፡፡

  ፍርግርግ ብረት ባልተነባበረበትና የበራቸውን ቁልፍ ታራሚዎች በሚዪዙበት ሃልደን ማረሚያ ቤት ታራሚዎች ለሚሰሩት ስራ በቀን 9 የአሜሪካን ዶላር ይከፈላቸዋል፡፡ በኖርዌይ የሞት ቅጣት ፍርድ የለም እንደውም ከፍተኛው የእስራት ጣሪያ 21 ዓመት ብቻ ነው፡፡
  ይህንን ሁሉ አስገራሚና አስደናቂ እንክብካቤ የሚያደርጉት እሾህን በሾህ ይሉት ብሒል ጠፍቷቸው ሳይሆን ታራሚዎች በሰሩት ጥፋታት ተፀፅተው ከጎበጡበት እንዲቀኑ የበደሉትን እንዲክሱና እንዲታረሙ ብቸኛው መንገድ በፍቅር መማረክ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ ደግሞም ሰርቶላቸዋል በአለም ዝቅተኛው የግድያ መጠን የሚከሰተው በኖርዌይ ነው፡፡
 • loader Loading content ...
 • @፩ ኢትዮጵያ   1 year ago
  Sewasewer
  ጋሽ መንግስቱ ለማ 'ባሻ አሸብር በ አሜሪካ ' በሚለው ግጥማቸው መሃል እንዲህ ይላሉ።
  ፖሊስ፡ ቢሮ፡ ሄድን፡ እሱ፡ ተለቀቀ፤
  አሸብር፡ ከልካይ፡ ግን፡ ወህኒ፡ ማቀቀ።
  በእውነቱ እኚህ አሸብር ከልካይ የተሰኙ በምናብ ሸራ ላይ የተሳሉ ግለሰብ እድለኛ አይደሉም ምክንያቱም አራዳ ግሪኮች እንደሚሸጡት ያለ ብስኩት አይተው ሊገዙ ጎራ ማለታቸው ያየ ዘረኛ ነጭ ብስኩት ሻጭ በጥቁርነታቸው መነሾ ቡጢ ማቅመሱ ሳያንስ ፖሊስ ቢሮ ሄደው እሱ ተለቆ እሳቸው በእስር መማቀቃቸው ክፉኛ የሚያስተዛዝብና ፍርደ-ገምድል ውሳኔ ነው። ፍትህ ሲዛባ በዳዮች የተበዳይነትን ጭንብል አጥልቀውና አይናቸውን በጨው አጥበው ከተፍ ይላሉ። ባለ ጸጋዎች በነዋያቸው ኃይል የእውነተኛ ፍትህን ቅጥር ይደፍራሉ። ሌቦች የዘረፋ አእምሮታቸው ከየትኛውም ግዜ በላይ ይሟሟቃል። ሰዎች ፍትህ ላይ ያላቸው ምልከታ የተንሸዋረረና አመኔታ ያጣ ይሆናል። የሀገሪቱ መሪ በነገሰበት መንበር ስርዓት አልበኝነትም በእኩሌታ ይነግሳል። በሀገሬ ኢትዮጵያም በፍትህ እጦት የሚሰቃዩና ለዘመናት በእግራችሁ አትምጡ እጃችሁ ይቅደም ተብለው በከንቱ የፍርድ ቤትን ደጃፍ የረገጡ እንዲሁም በመርገጥ ላይ ያሉ ሁሉ ክፉኛ ያሳዝኑኛል።  እናም በፍትህ ስርዓት ውስጥ ለምትገኙ ሁሉ አንድ መልዕክት አለኝ። ፍትህ! ፍትህ! ፍትህ! በጥቅም ያልተደለለ፣ በዝምድና ያልተንሸዋረረና ህግና ህግን ብቻ መሠረት ያደረገ እውነተኛ ፍትህ ስጡን።
 • loader Loading content ...
loader Loading content ...

Comments (0)


  This user has no comment yet.