loader

Topics (1)


loader Loading content ...

Explanations (1)


 • @Endalk   2 years ago
  Sewasewer

  ኢትዮጵያ ረዥም ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ካላቸዉ ሀገራት አንዷናት፡፡ በዚህ ረዥም ታሪኳ ዉስጥ ህዝቦቿ ሲተዳደሩበት የነበረ የራሷ የሆነ የህግ እና የህግ ስርዓት የነበራት ሀገር ነች፡፡

 • loader Loading content ...
loader Loading content ...

Comments (1)


 • @Endalk   2 years ago
  Sewasewer
  የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ዘመን ደብተራዎችና ፈጠራዎቻቸው - - - Read PDF

  ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ [1000 ዓ.ዓ ገዳማ] ደርግ እስከ መጣበት ድረስ በኢትዮጵያ ሲገዛ የኖረ መንግሥት ነው። መሠረቱ አክሱም ሆኖ እስከ ዛጉዬ ሥርወ መንግሥት [ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን] ድረስ በአክሱሞች ተይዞ ቆይቷል። የላስታ መንግሥት ዛጉዬ በመባል ይታወቃል "ዘአጕየየ መንግስተ አክሱም" ለማለት ነው። ከዘጠነኛው እስከ አሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገዝቶ አስደናቂ ቅርሶችን አስቀምጦ አልፏል። የዛጕየ ዘመነ መንግሥት ማክተም ምክንያቱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መሆናቸው ታውቋል። ገድለ ተክለ ሃይማኖት እንደሚለው ላስታዎች መንግሥት አይገባቸውም ነበር። ምክንያቱን ሲያቀርብ "የሰሎሞን ዘር ስላልሆኑ" ይላል። ስለዚህ መንግሥት ወደ ሰሎሎሞን ዘር ወደ ይኩኖ አምላክ ሲዛወር ክህነትም የአሮን ዘር ወደ ሆኑት ወደ ተክለ ሃይማኖት ተዛወረ፣ ከተክለ ሃይማኖት ዘር ውጭ ጳጳስ ወይም እጨጌ መሾም እርግማን ነው በማለት ገድላቸው ይደመድማል። ሃይማኖት የፖለቲካ መሳሪያ መሆን የጀመረው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው። አቡነ ተክለ ሃይማኖት "የሰሎሞን ሥርወ መንግሥት ወደ ትክክለኛው ዘር ወደ ይኩኖ አምላክ መመለስ አለበት" እያሉ ሲሰብኩ ኖረው በመጨረሻ ስብከቱ አላዋጣ ሲል የላስታው ንጉሥ በጦር እንዲገደል ቀጥተኛ ትዛዝ መስጠታቸውን ገድላቸው ይናገራል።[ገድለ ተክለ ሃይማኖት ም 24፥1-5 እና ም 26ን ያንቡ]

       የላስታው ንጉሥ ይትባረክ በይኩኖ አምላክ ሲገደል ወሎ ውስጥ ከላስታ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው "ድግር መጥረቢያ" ላይ የበርካታ ሰዎች እግር መቆረጡን በአካባቢው ታሪክ ሆኖ ይነገራል። አገሩ "ድግር መጥረቢያ" የተባለበት ምክንያት እግር የተቆረጠበት ቦታ በመሆኑ ነው ይባላል። ይህ ጉዳት ያገኛቸው ሰዎች ግን ያች እግር የተቆረጠው "በጸሎት ብዛት" መሆኑን ይተረካሉ። ነገሩ የፖለቲካ ጨዋታ ስለሆነ ማለባበስ የሚያስፈልገው በመሆኑ ነው እንዲህ የተባለው የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ። ሃይማኖትን የፖለቲካ መሳሪያ ማድረግ እንደሚቻል ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት የተማሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም በአሜሪካ ቁጭ ብለው ደርግን በኢሕዴግ ሲያስወጉ እንደነበር ይተረክላቸዋል። እርሳቸው ግን አሜሪካ ስለነበሩ እግራቸው በመጥረቢያ ከመቆረጥ ተርፏል። ስለዚህ ስድስት ክንፍ ማውጣት አያስፈልጋቸውም መብረር ከፈለጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተከራያቸው በራሪ አካላት አሉ።     ስድት ክንፍ የወጣላቸው ሰው እግር ስለሌላቸው ነው ተብሏል እናም በክንፋቸው በረው ሄደው በ24ቱ ካህናተ ሰማይ ላይ ተደረብው 25ኛ ካህን ሆነው እስከ ዛሬ ድረስ የጌታን መንበር እያጠኑ ነው ተብሏል። አንድ ቀን ሰውየው ክንፍ ያወጡት በሥጋቸው ነው ወይስ በነፍሳቸው ብዬ ጠይቄ ነበር። በነፍሳቸው ነው ተባልሁ። ታዲያ ደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ነው ክንፉ የበቀለው ብሎ ገድላቸው ለምን ይናገራል? ስላቸው አይ ይቅርታ በሥጋቸው ነው አሉኝ። በሥጋቸው ከሆነ በደብረ ሊባኖስ ከሚገኘው አጥንታቸው ላይ ክንፋቸውንም አብረን ልናገኘው እንችላለን ስላቸው ክንፋቸው ተሰውሯል ብለውኝ አረፉት። ተሠውሯል? ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀልስ እንዴት ነው ስላቸው አዎ ለክብራቸው ነው አሉኝ ። ሌላው እውነተኛው አባት ግን ልጄ እንግሊዛዊቷ ንግስት ለአጼ ምኒልክ ባለቤት የሸለሟቸው ስጦታ ነው ብለው እውነቱን ነገሩኝ። አዳዲስ ውሸቶች በጥንቱ ውሸት ላይ እየተጨመሩ አስቸግረውናል ብለውም አከሉልኝ እኔ ግን የፖለቲካ ጉዳይ ነው እላለሁ።     መለስና ይኩኖ አምላክ፤ አቡነ ጳውሎስና አቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ ነጉሥ ይትባረክና መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ይመሳሰሉብኛል። ይኩኖ አምላክ ተክለ ሃይማኖት ለዋሉት ውለታ ሲሶ መንግሥት የሰጣቸው ሲሆን፤ መለስም ለአቡነ ጳውሎስ ይኸው ፕትርክናውን ከአቡነ መርቆርዮስ ቀምቶ አጎናጽፏቸው ይገኛል። ክህነት ከአሮን ዘር ወጣ ማለት ነው?። ይትባረክ ድግር መጥረቢያ ላይ፤ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዝምባዌ ላይ ወድቀው ቀሩ። ሃይማኖት እስከ አሁን ድረስ የፖለቲካ ጨዋታውን ሞቅ ሞቅ አርጎታል።  ማህበረ ቅዱሳንም ከዚህ ታሪክ በመኮረጅ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤ ፍጻሜውን ወደ ፊት የምናየው ይሆናል። እያንዳዱን የጨዋታ ዓይነት ወደ ፊት እመለስበታለሁ። ዛሬ ላሳያችሁ የምፈልገው የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ደብተራዎች የፈጠሩትን እና የቤተ ክርስቲያናችን እምነት ያደረጉትን ጥንታዊ ተረት ነው።

   ተረቱ ባጭር ቃል፦ትንሽ መነሻ ካገኙ እግራቸውን ወደ ላይ ብለው ውሸታቸውን በመልቀቅ የሚታወቁት የሰሎሞን ሥርወ መንግሥት ደብተራዎች ማፈሪያ የሆነውን ተረት ሲተርቱ እንዲህ ይላሉ።   የኢትዮጵያ ንግሥት ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ለማየት በሄደችበት ጊዜ[ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው 1ነገ 10] ከሰሎሞን ጸንሳ መመለሷንና ቀዳማዊ ምኒልክን እንደወለደች ይተረካል። ምኒልክ በተወለደ በሃያ ዓመቱ አባቱን ለመጎብኘት ሄዶ ነበር። ሲመለስ ልጄን ባዶ እጄን አልሰደውም ብሎ ታቦተ ሚካኤል ከሦስት መቶ በላይ የሆኑ ሌዋውያን ከልዩ ልዩ መጻሕፍት ጋር እንዲሰጠው ታዘዘለት። ሌዋውያኑ ግን በሚካኤል ፈንታ ታቦተ ጽዮንን ሰርቀው ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ታቦተ ጽዮን በኢትዮጵያ እንደምትገኝ ይተርካሉ። የመንግሥታቸው ታሪክ ከዚህ እንደሚጀምርና ንጉሥነትም ከይሁዳ ዘር አይወጣም የተባለውን የጌታ ቃል በመጥቀስ "ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ" ብለው ሰይመው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲገዙበት እንደኖሩ ሁላችን የምናውቀው ጉዳይ ነው። ይህ ያለፈ ታሪክ ዛሬ አይቆጨንም ነገር ግን ዛሬ ላይ ለምንገኝ ኢትዮጵያውያንን መናፍቅ እያሰኘ እያስወገረን ስለሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀውና ፍርዱን እንዲሰጥ እንፈልጋለን። አትስረቅ የሚለው ሕግ የተጻፈበት ጽላት የተቀመጠበት ታቦት ተሰርቆ መጣ የሚለው ታሪክ የተጋነነ ነው። እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ታቦት አንድ ብቻ ነው ዘጸ 25፥10-28። የሚካኤል ታቦት አብሮ እንደተሰጠው የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የለም። በታሪክም በአዋልድ መጻሕፍትም ስለሚካኤል ታቦት የሚናገር አይገኝም ከድርሳነ ኡራኤልና ከገድለ ተክለሃይማኖት በቀር።  በእርግጥ ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መጣለችን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለታቦተ ጽዮን ምን ይላል?                                                        መጽሐፍ ቅዱሳዊው ታቦት

                                                     የኢትዮጵያው ታቦት

  መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ታቦትና የኢትዮጵያውን ታቦት ተመልከቱ   ምኒልክና የሰሎሞን ዘመን መራራቅ

  1ኛ ሰሎሞን በነገሰ በአራተኛው ዓመት ከሁለት ወር ቤተ መቅደሱን ለመስራት መሠረት አኖረ። 1 ነገ 6፥1 2ዜና 3፥1-22ኛ. የቤተ መቅደሱ ሥራ ሶሎሞን በነገሰ በ11ኛው ዓመት ከ8 ወር ተጠናቀቀ። 1ነገ 6፥36-37 ሥራው የፈጀው ጊዜ 7 ዓመት ከስድስት ወር ነው።3ኛ. በጥቅሉ የራሱን ቤት እና ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የፈጀበት ጊዜ 20 ዓመት ነው 1ነገ 9፥10 2ዜና 8፥1-8። ከዚህ በኋላ ነበር ንግሥተ ሳባ የሶሎሞንን ዝና ሰምታ ለመጎብኘት የሄደችው መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ መቅደሱን እና የቤቱን ሥራ እንደጎበኘች ይናገራልና ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ መሄዷን ለመረዳት አንቸገረም 1ነገ 10፥1-13። 2ዜና 9፥1-12።4ኛ. ንግሥቲቱ ወደ ሶሎሞን ለመድረስ የፈጀባት ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ባናውቅም በደረሰች ጊዜ ጸነሰች ብለን እንኳ ብናስብ የጽንሱ ጊዜ 9 ወር ነው።5ኛ. እንደ ክብረ ነገሥቱ እንደ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ትረካ ቀዳማዊ ምኒልክ ከ20 ዓመት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ 3 ዓመት ቆይቶ ተመልሷል ስለሚል በድምሩ 23 ይሆናል። ጠቅላላ ድምር ቤተ መቅደሱ ከመጀመሩ በፊት የነበረው ይሰሎሞን የንግሥና ዘመን 4 ዓመት ከ2 ወር   የቤተ መቅደሱና የራሱ ቤት ሥራ የፈጀው ጊዜ 20 ዓመት  20+4= 24  ምኒልክ የተጸነሰበት ጊዜ 9 ወር 9+2 = 11 ወር ይሆናልምኒልክ ኢትዮጵያ የቆየበት ጊዜ 20 ዓመት እና አባቱ የቆየበት 3 ዓመት 20+3= 23ጠቅላላ ድምሩ 47 ዓመት ከ11 ወር ይሆናል።  48 አመት ብንለው ይሻላል።   መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳን ግን ሰሎሞን የነገሰው 40 ዓመት ብቻ እንደሆነና እንደሞተ ነው። በመጽሐፍ ቅዱሱ መሠረት ምኒልክ የሄደው ሰሎሞን በሞተ በ5ኛው ዓመት ነው። ታዲያ ሰሎሞን እና ምኒልክ አራባና ቆቦ ሆነው ሳለ እንዴት በሰሎሞን ትዕዛዝ ሌዋውያንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ ሊመጣ ቻለ? ነገሩ ተረት መሆኑን እንረዳለን። ክብረ ነገሥት በቤተ መቅደሱ ከነበሩት ታቦታት ውስጥ አንዱ የማርያም አንዱ የሚካኤል ነበር ይልና የሚካኤልን ውሰድ ቢባል የሚካኤልን በማርያም ሥፍራ ተክተው የማርያምን ይዘው መጡ ይላል። ማርያም በሰሎሞን ጊዜ ነበረችን? ገና መች ተወለደችና ነው ታቦት የሚቀረጽላት? በሬው ወለደዎች! በመሠረቱ ታቦተ ጽዮን ከሰሎሞን በኋላ 16ኛ ሆኖ በነገሰው በኢዮስያስ ዘመን እዚያው ኢየሩሳሌም እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ታሪኩን እንደዚህ እናስተውለውበመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው የታቦተ ጽዮን ታሪክ በማያሻማ መልኩ ወደ ባቢሎን ተማረከ የሚል ነው

   ታቦቱ ከመማረኩ በፊት በኢየሩሳሌም እንደነበረ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል "ቅዱሱን ታቦት የእሥራኤል ንጉሥ  የዳዊት ልጅ ሰሎሞን  ባሠራው  ቤት ውስጥ አኑሩት ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም" 2ዜና 35፡3 ንጉሥ ኢዮስያስ የተናገረው   ( ኢዮስያስ ለሰሎሞን አሥራ ስድስተኛ ንጉስ ነበር) ። ከኢዮስያስ በፊት ነግሶ የነበረው ምናሴ  የቤተ መቅደሱን ዕቃ አውጥቶ  በውስጡ  ጣኦት አስቀምጦበት እንደነበር  2ዜና 33፡8 ላይ ይናገራል። በዚህ ምክንያት ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው በየቤታቸው  ይዞሩ ነበር ። ኢዮስያስ "ከንግዲህ ወዲህ በትክሻችሁ ሸክም አይሁንባችሁ" ያለው በዚህ ምክንያት ነው።

      የባቢሎን ምርኮ ከኢዮስያስ ዘመን በኋላ [600 ዓ.ዓ]ተጀምሮ በሴዴቅያስ ዘመን ተፈጽሞአል። በባቢሎን የምርኮ ዘመን የነበረው ነቢይ ኤርምያስ ነበር።2ዜና 36፡11-23    ነቢዩ ኤርምያስ ስለታቦቱ በራሱ መጽሐፍም እንዲህ ብሎአል"የግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከንግዲህ ወዲህ አይጠሩም ልብ አያደርጉትም አያስቡትምም አይሹትምም፤ከንግዲህወዲህም አይደረግምም" ኤር 3፡16። ኤርምያስ ከኢዮስያስ ጀምሮ እስከ ባቢቢሎን ምርኮ እስከ ሴዴቅያስ የነበረ ነቢይ ነው  ኤር1፡1-3ን ያንቡ። ኤርምያስ "ከእንግዲህ ወዲህ አይደረግም" ያለው ታቦቱ በባቢሎናውያን እንደሚወሰድ በመንፈስ ቅዱስ ስለተረዳ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ከተወሰደ ከ330 ዓመት በኋላ እንዲህ ሊናገር አይችልም። ኢዮስያስ ያልነበረን ታቦት በቤተ መቅደስ አኑሩት በትክሻችሁ አትሸከሙት ሊል እንደማይችል ሁሉ ኤርምያስም በዘመኑ የነበረውን ታቦት ትንቢት ተናግሮበታል።     ታቦቱ በሴዲቅያስ ዘመን ወደ ባቢሎን እንደተወሰደ የሚናገረው  የመጽሐፍ   ቅዱስ ክፍል የሚከተለው ነው። "እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበትን ንዋየ ቅድሳቱን ጥቃቅኑን እና ታላቁን ዕቃ ሁሉ የግዚአብሔር ማደሪያ ታቦትንም ከቤተ መንግሥት እቃ ቤትም  ያለውን ሳጥኑንም ሁሉ  ማርከው ወደ ባቢሎን ወሰዱ" እዝራ ካልእ 15፥4

  "ቤተ መቅደሳችን እንደፈረሰ አታይምን ግናይቱ እንደጠፋ ምስጋናችን እንደቀረ ዘመራ ዘውዳችን እንደወደቀ ተድላ ደስታችን እንደጠፋ የሕጋችን ማደሪያ ታቦተ ጽዮን እንደተማረከች አታይምን?" እዝራ ሱቱ 9፥ 23።

  "ከዚህ ሁሉ የሚበልጥ ታቦተ ጽዮን እንደ ጠፋች ቀረች ከሷ ጋርም ንዋየ ቅድሳቱ ተማርኮ ሄደ በጠላቶቻችን በባቢሎናውያን እጅ ወደቅን" እዝራ ሱቱ 9፥ 23።      ከዚህ ትምህርት  እንደምንረዳው  መጽሐፍ ቅዱሱና ክብረ ነገስቱ፤ ገ/ተክለ ሃይማኖት፤ድርሳነ ኡራኤል አለመስማማታቸውን ነው።  ምክንያቱም  ሦስቱ መጻህፍት ማለት ክብረ ነገሥት፣ ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ ድርሳነ ኡራኤል፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በማደም በሰሎሞን ጊዜ ታቦቱ ተሰርቆ መጧል ሲሉ  የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ግን ወደባቢሎን ተማርኳል ይላል። በትውፊት የሚያላክኩ ደብተራዎችን እንቀባላቸው ብንል እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚቀድም መጽሐፍ የለምና ዘወር በሉ ለማለት እንገደዳለን። ከላይ የጠቀስሗቸውን ጥቅሶች ለማግኘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቀኖናዋ የተቀበለችውን ሰማኒያ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ይመልከቱ።

  ማህበረ ቅዱሳን ያሳተመው "ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ" የሚለው መጽሐፍ ግን ታቦቱ በሰሎሞን ጊዜ ሳይሆን  በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ወደ ግብጽ በተሰደዱ ካህናተ ኦሪት  ለዘመናት ግብጽ ቆይቷል ከዚያም ስደት ሲበዛባቸው ወደ ሱዳን ይዘውት እንደ መጡ ፤ ከሱዳን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ይዘውት እንደገቡ ይተርካል ።በጣና ቂርቆስ ለ800 መቶ አመት ያህል ቆይቶ  የአክሱም ነገሥታት  ከአይሁድ ነጥቀው  እንደወሰዱትና በአክሱም እንዳስቀመጡት፤ እንዲሁም  በዮዲት ጦርነት ጊዜ ወደ ዝዋይ ተወስዶ ቆይቶ  ዮዲት ከተሸነፈች በኃላ ወደ አክሱም ተመልሶ  አሁንም በዚያ እንደሚገኝ መጽሐፉ ይተርካል።ይህ ትረካ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይመሳሰላል፤ ፍርዱን ግን ለአንባቢ እንተወዋለን።

   ማጠቃለያ ነገሩ የፖለቲካ ጭዋታ መሆኑን ደርሰንበታል፣ እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሕዝባችንን ለመግዛት ታቅዶ የተፈለሰፈ ታሪክ መሆኑን ለማንም ግልጥ ነው። መንግሥት ከይሁዳ ዘር አይወጣም የሚለውን ቃል የሚያከብረው ሕዝባችን የሁዳ መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስ መወረሱን እርሱም የዘላለም ንጉሳችን መሆኑን ሳይነግሩት ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንዲሉ የይሁዳ ዘር እኛ ነን ከሰሎሞን ተወልደናል እናም መንግሥታችንን ማንም እንዳይነካ የአሮን ዘር ስለሆንን ክህነትም የኛ ነው ቃሉን መጠበቅ አለባችሁ በማለት የጌታን ክብር ሠውረው የራሳቸውን ንግሥና ሲያመቻቹ ኖረዋል። በዚህ ምክንያት ነው ይህ ተረት እንዲፈጠር የተደረገው።    ዛሬ ግን የጽድቅ ጸሐይ ወጥታለች። ይህ እንደሃይማኖት ሆኖ የቆየው ታሪክ ተረት መሆኑን የደረሱበት ከዘር፣ ከፖለቲካ ነጻ የሆኑ፣ ወንጌልን ከእውነት ጋር እንደ ዝናር የታጠቁ የለውጥ ሐዋርያት ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን አፍርታለች። ለውሸት ለጣኦት ለማንኛውም የሥጋ ሥራ ርኅራኄ የላቸውም፣ ለማፍረስና ለመሥራት፤ ለመንቀልና ለመትከል እግዚአብሔር ልኳቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ማሳመን ያቃታቸው፣ ለዘመናት ሲሰብኩት የኖሩት ተረት እየተናደ ከላያቸው ላይ የወደቀባቸው ቢጽ ሀሳውያን ግን በጩቤ መዋጋት ጀምረዋል። ሰይፋቸውን ወደ ሰገባቸው ከተው ወንጌልን እንዲቀበሉ፤ ኋላ ቀር የሆነውንና ሃይማኖትን የፖለቲካ መሣሪያ አድርጎ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ሲጎትት የኖረውን ተረት ተረት እንዲጥሉት ጥሪ እናቀርባለን። ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ ፖለቲካን ማራመድ ብጥብጥን እንጂ ሰላምን አያመጣም።
loader Loading content ...